መዝሙር 101 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ትክክለኛ አስተዳደር

የዳዊት መዝሙር

1. ስለ ምሕረትና ስለ ፍትሕ እዘምራለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለአንተ በምስጋና እቀኛለሁ።

2. እንከን የማይገኝባትን መንገድ አጥብቄ እይዛለሁ፤አንተ ወደ እኔ የምትመጣው መቼ ነው?በቤቴ ውስጥ፣በንጹሕ ልብ እመላለሳለሁ።

3. በዐይኔ ፊት፣ክፉ ነገር አላኖርም።የከሓዲዎችን ሥራ እጠላለሁ፤ከእኔም ጋር አይጣበቅም።

4. ጠማማ ልብ ከእኔ ይርቃል፤ለክፋትም ዕውቅና አልሰጥም።

5. ባልንጀራውን በስውር የሚያማውን፣አጠፋዋለሁ፤ትዕቢተኛ ዐይንና ኵራተኛ ልብ ያለውን፣እርሱን አልታገሠውም።

6. ከእኔ ጋር ይኖሩ ዘንድ፣ዐይኖቼ በምድሪቱ ታማኞች ላይ ናቸው፤በንጽሕና መንገድ የሚሄድ፣እርሱ ያገለግለኛል።

7. አታላይ የሆነ ማንም ሰው፣በቤቴ ውስጥ አይኖርም፤ሐሰትን የሚናገር፣በፊቴ ቀና ብሎ አይቆምም።

8. በምድሪቱ ላይ ያሉትን ክፉዎች ሁሉ፣በየማለዳው አጠፋቸዋለሁ፤ክፉ አድራጊዎችንም ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር ከተማ እደመስሳቸዋለሁ።