መዝሙር 75 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለመለኮታዊው ዳኛ የቀረበ ዝማሬ

ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዜም፤ የአሳፍ መዝሙር ማሕሌት

1. አምላክ ሆይ፤ ምስጋና እናቀርብልሃለን፤ስምህ ቅርብ ነውና ምስጋና እናቀርብልሃለን፤ሰዎችም ስለ ድንቅ ሥራህ ይናገራሉ።

2. አንተም እንዲህ አልህ፤ “ለይቼ በወሰንኋት ሰዓት፣በቅን የምፈርድ እኔ ነኝ።

3. ምድርና ሕዝቦቿ ሁሉ በሚናወጡበት ጊዜ፣ምሰሶቿን አጽንቼ የምይዝ እኔ ነኝ። ሴላ

4. እብሪተኛውን፣ ‘አትደንፋ’፤ክፉውንም ‘ቀንድህን ከፍ አታድርግ እለዋለሁ፤

5. ቀንድህን ወደ ሰማይ አታንሣ፤ዐንገትህንም መዝዘህ አትናገር።’ ”

6. ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ፣ወይም ከምድረ በዳ አይመጣምና፤

7. ነገር ግን የሚፈርድ እግዚአብሔር ነው፤እርሱ አንዱን ዝቅ፣ ሌላውን ከፍ ያደርጋል።

8. በእግዚአብሔር እጅ ጽዋ አለ፤በሚገባ የተቀመመና ዐረፋ የሚወጣው የወይን ጠጅ ሞልቶበታል፤ይህን ከውስጡ ወደ ውጭ ገለበጠው፤የምድር ዐመፀኞችም አተላው ሳይቀር ይጨልጡታል።

9. እኔ ግን ይህን ለዘላለም ዐውጃለሁ፤ለያዕቆብም አምላክ ዝማሬ አቀርባለሁ።

10. የክፉዎችን ሁሉ ቀንድ እሰብራለሁ፤የጻድቃን ቀንድ ግን ከፍ ከፍ ይላል።