መዝሙር 67 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የመከር ጊዜ መዝሙር

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች የሚዘመር፤ የዳዊት መዝሙር፤ ማኅሌት

1. እግዚአብሔር ይማረን፤ ይባርከን፤ፊቱንም በላያችን ያብራ፤ ሴላ

2. መንገድህ በምድር ላይ፣ማዳንህም በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይታወቅ ዘንድ።

3. እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰዎች ያመስግኑህ፤ሰዎች ሁሉ ምስጋና ያቅርቡልህ።

4. ለሕዝቦች በቅን ስለምትፈርድላቸው፣ሰዎችንም በምድር ላይ ስለምትመራ፣ሕዝቦች ደስ ይበላቸው፤ በእልልታም ይዘምሩ። ሴላ

5. እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰዎች ያመስግኑህ፤ሰዎች ሁሉ ምስጋና ያቅርቡልህ።

6. ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።

7. እግዚአብሔር ይባርከናል፤የምድርም ዳርቻዎች ሁሉ እርሱን ይፈሩታል።