መዝሙር 12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከክፉ ዓለም ለመዳን የቀረበ ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ በስምንተኛው ቅኝት የሚዘመር፤ የዳዊት መዝሙር።

1. እግዚአብሔር ሆይ፤ ደግ ሰው የለምና አንተው ድረስልኝ!ከሰዎችም መካከል አንድ ታማኝ አይገኝም።

2. እርስ በርሳቸው ውሸት ይነጋገራሉ፤በሽንገላ ከንፈርና በሁለት ልብ ይናገራሉ፤

3. ሸንጋዩን ከንፈር ሁሉ፣ነገር የምታበዛውንም ምላስ እግዚአብሔር ያጥፋ!

4. እነዚህም፣ “በአንደበታችን እንረታለን፤ከንፈራችን የእኛ ነው፤ ጌታችንስ ማነው?”የሚሉ ናቸው።

5. እግዚአብሔር፣ “ስለ ድኾች መከራ፣ስለ ችግረኞችም ጩኸት፣አሁን እነሣለሁ፤በናፈቁትም ሰላም አኖራቸዋለሁ” ይላል።

6. የእግዚአብሔር ቃል የጠራ ቃል ነው፤ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ፣በምድር ላይ በከውር እንደ ተፈተነ ብር ነው።

7. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ትጠብቀናለህ፤ከዚህም ትውልድ ለዘላለም ትከልለናለህ።

8. በሰዎች ዘንድ ክፋት ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ፣ዐመፀኞች በየአቅጣጫው በዛቻ ይዞራሉ።