መዝሙር 54 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለፍትሕ አምላክ የቀረበ አቤቱታ

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ዜፋውያን ወደ ሳኦል መጥተው፣ “ዳዊት በእኛ ዘንድ ተደብቆአል” ባሉት ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት።

1. እግዚአብሔር ሆይ፤ በስምህ አድነኝ፤በኀይልህም ፍረድልኝ።

2. እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማልኝ፤የአፌንም ቃል አድምጥ።

3. ባዕዳን ተነሥተውብኛልና፤ግፈኞች ነፍሴን ሽተዋታል፤እግዚአብሔርንም ከምንም አልቈጠሩም። ሴላ

4. እነሆ፤ እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፤ጌታም ደግፎ ይይዘኛል።

5. የገዛ ክፋታቸው በሚያደቡብኝ ላይ ይመለስባቸው፤በቃልህ ታማኝ ነህና አጥፋቸው።

6. በበጎ ፈቃድ መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ መልካም ነውና፣ለስምህ ምስጋና አቀርባለሁ፤

7. ከመከራ ሁሉ ታድጎኛልና፤ዐይኔም የጠላቶቼን ውድቀት ለማየት በቅቶአል።