መዝሙር 1 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አንደኛ መጽሐፍ

ሁለቱ መንገዶች

1. በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፣ሰው ብፁዕ ነው።

2. ነገር ግን ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል።

3. እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።

4. ክፉዎች ግን እንዲህ አይደሉም፤ነገር ግን ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው፣ገለባ ናቸው።

5. ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ ፊት፣ኀጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር መቆም አይችሉም፤

6. እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ይጠብቃልና፤የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።