መዝሙር 138 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የምስጋና መዝሙር

የዳዊት መዝሙር

1. እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤በአማልክት ፊት በመዝሙር እወድስሃለሁ።

2. ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ስለ ምሕረትህና ስለ ታማኝነትህ፣ለስምህ ምስጋና አቀርባለሁ፤ስምህንና ቃልህን፣ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አድርገሃልና።

3. በጠራሁህ ቀን መልስ ሰጠኸኝ፤ነፍሴን በማደፋፈርም ብርቱ አደረግኸኝ።

4. እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፍህን ቃል በሰሙ ጊዜ፣ የምድር ነገሥታት ሁሉያመስግኑህ።

5. የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና፣ስለ እግዚአብሔር መንገድ ይዘምሩ።

6. እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል።

7. በመከራ መካከል ብሄድም፣አንተ ሕይወቴን ትጠብቃታለህ፤በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጅህን ትዘረጋለህ፤በቀኝ እጅህም ታድነኛለህ።

8. እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያለውን ዐላማ ይፈጽማል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ለዘላለም ነው።የእጅህንም ሥራ ቸል አትበል።