መዝሙር 126 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የስደት ተመላሾች መዝሙር

መዝሙረ መዓርግ

1. እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፣ሕልም እንጂ እውን አልመሰለንም።

2. በዚያን ጊዜ አፋችን በሣቅ፣እንደበታችንም በእልልታ ተሞላ፤በዚያን ጊዜም በሕዝቦች መካከል፣“እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገላቸው” ተባለ።

3. እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገልን፤እኛም ደስ አለን።

4. እግዚአብሔር ሆይ፤ በነጌቭ እንዳሉ ጅረቶች፣ምርኳችንን መልስ።

5. በእንባ የሚዘሩ፣በእልልታ ያጭዳሉ።

6. ዘር ቋጥረው፣እያለቀሱ የተሰማሩ፣ነዶአቸውን ተሸክመው፣እልል እያሉ ይመለሳሉ።