መዝሙር 14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አምላክ የለሽ ሰዎች

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1. ሞኝ በልቡ፣“እግዚአብሔር የለም” ይላል።ብልሹዎች ናቸው፤ ተግባራቸውም ጸያፍ ነው፤በጎ ነገር የሚሠራ አንድም የለም።

2. የሚያስተውል፣ እግዚአብሔርን የሚፈልግ መኖሩን ለማየት፣ እግዚአብሔር ከሰማይ ወደ ሰው ልጆች ተመለከተ።

3. ሁሉም ከመንገድ ወጥተዋል፤በአንድ ላይም ብልሹ ሆነዋል፤አንድ እንኳ፣መልካም የሚያደርግ የለም።

4. የእግዚአብሔርን ስም የማይጠሩት፣ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉት፣ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ዕውቀት የላቸውምን?

5. ባሉበት ድንጋጤ ውጦአቸዋል፤እግዚአብሔር በጻድቃን መካከል ይገኛልና።

6. እናንተ የድኾችን ዕቅድ ለማፋለስ ትሻላችሁ፤ እግዚአብሔር ግን መጠጊያቸው ነው።

7. ምነው እስራኤልን የሚያድን ከጽዮን በወጣ! እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በሚመልስበት ጊዜ፣ያዕቆብ ደስ ይበለው፤ እስራኤልም ሐሤት ያድርግ።