መዝሙር 124 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእስራኤል አዳኝ

የዳዊት መዝሙረ መዓርግ

1. እስራኤል እንዲህ ይበል፦“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ኖሮ፣

2. ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ኖሮ፣

3. ቍጣቸው በላያችን በነደደ ጊዜ፣በቁመናችን በዋጡን ነበር፤

4. ጐርፍ ባጥለቀለቀን፣ፈረሰኛው ውሃ ባሰጠመን፣

5. ደራሽ ውሃም ጠራርጎ በወሰደን ነበር።

6. በጥርሳቸው ከመዘንጠል የጠበቀን፣ እግዚአብሔር ይባረክ።

7. ነፍሳችን እንደ ወፍ፣ከዐዳኝ ወጥመድ አመለጠች፤ወጥመዱ ተሰበረ፤እኛም አመለጥን።

8. የሰማይና የምድር ፈጣሪ፣ የእግዚአብሔር ስም ረዳታችን ነው።