መዝሙር 111 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለመለኮቱ ባሕርያት የቀረበ ጸሎት

1. ሃሌ ሉያ።በቅኖች ሸንጎ፣ በጉባኤም መካከል፣ ለእግዚአብሔር በፍጹም ልቤ ምስጋና አቀርባለሁ።

2. የእግዚአሔር ሥራ ታላቅ ናት፤ደስ የሚሰኙባትም ሁሉ ያውጠነጥኗታል።

3. ሥራው ባለ ክብርና ባለ ግርማ ነው፤ጽድቁም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

4. ድንቅ ሥራው ሲታወስ እንዲኖር አደረገ፤ እግዚአብሔር ቸር፣ ርኅሩኅም ነው።

5. ለሚፈሩት ምግብን ይሰጣል፤ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።

6. ለሕዝቡ የአሕዛብን ርስት በመስጠት፣የአሠራሩን ብርታት አሳይቶአል።

7. የእጁ ሥራ እውነተኛና ቅን ነው፤ሥርዐቱም ሁሉ የታመነ ነው፤

8. ከዘላለም እስከ ለዘላለም የጸና ነው፤በእውነትና በቅንነትም የተሠራ ነው።

9. ለሕዝቡ መዳንን ሰደደ፤ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤ስሙም የተቀደሰና የተፈራ ነው።

10. እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፤ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።