መዝሙር 114 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለፋሲካ የቀረበ ውዳሴ

1. እስራኤል ከግብፅ ወጥቶ ሲሄድ፣የያዕቆብም ቤት ቋንቋው ልዩ ከሆነ ሕዝብ ተለይቶ ሲወጣ፣

2. ይሁዳ የእግዚአብሔር መቅደስ፣እስራኤልም ግዛቱ ሆነ።

3. ባሕር አየች፤ ሸሸችም፤ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ።

4. ተራሮች እንደ አውራ በግ፣ኰረብቶችም እንደ ጠቦት ዘለሉ።

5. አንቺ ባሕር፤ የሸሸሽው አንቺም ዮርዳኖስ ያፈገፈግሽው ለምንድን ነው?

6. እናንተ ተራሮች እንደ አውራ በግ፣ኰረብቶችም እንደ ጠቦት ለምን ዘለላችሁ?

7. ምድር ሆይ፤ በጌታ ፊት፣በያዕቆብ አምላክ ፊት ተንቀጥቀጪ፤

8. እርሱ ዐለቱን ወደ ኩሬ፤ቋጥኙንም ወደ ውሃ ምንጭ ለወጠ።