መዝሙር 47 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር፣ የእስራኤል ንጉሥ የዓለም ጌታ

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር።

1. ሕዝቦች ሁላችሁ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፤ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር እልል በሉ።

2. በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ፣ልዑል እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነውና።

3. ሕዝቦችን ከእኛ በታች አደረገ፤መንግሥታትንም ከእግራችን ሥር አስገዛልን።

4. ለሚወደው ለያዕቆብ ክብር የሆነችውን፣ርስታችንን እርሱ መረጠልን። ሴላ

5. አምላክ በእልልታ፣ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።

6. አምላካችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤ንጉሣችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤

7. እግዚአብሔር የምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፤ምርጥ ዝማሬ አቅርቡለት።

8. እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ነግሦአል፤እግዚአብሔር በተቀደሰ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦአል።

9. ከአብርሃም አምላክ ሕዝብ ጋር፣የሕዝቦች መኳንንት ተሰበሰቡ፤የምድር ነገሥታት የእግዚአብሔር ናቸውና፤እርሱም እጅግ ከፍ ከፍ ያለ ነው።