7. የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤አንተ ቅን የሆንህ ሆይ፤የጻድቃንን መንገድ ታቃናለህ።
8. እግዚአብሔር ሆይ፤ በሕግህ ጐዳና በመሄድ፣አንተን ተስፋ አድርገናል፤ስምህና ዝናህ፣የልባችን ምኞት ነው።
9. ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፤መንፈሴም በውስጤ ትፈልግሃለች።ፍርድህ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ፣የዓለም ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ።
10. ክፉዎች ርኅራኄ ቢደረግላቸው እንኳ፣ጽድቅን አይማሩም፤በቅንነት ምድር እንኳ ክፋትን ያደርጋሉ፤ የእግዚአብሔርንም ግርማ አያስተውሉም።
11. እግዚአብሔር ሆይ፤ ክንድህ ከፍ ከፍ ብሎአል፤እነርሱ ግን አላስተዋሉም፤ለሕዝብህ ያለህን ቅናት ይዩ፤ ይፈሩም፤ለጠላቶችህም የተዘጋጀው እሳት ይብላቸው።
12. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰላምን መሠረትህልን፤የሠራነውንም ሁሉ አንተ አከናወንህልን።
13. እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ከአንተ ሌላ ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤እኛ ግን የአንተን ስም ብቻ እናከብራለን።
14. እነርሱ ሞተዋል፤ ከእንግዲህ በሕይወት አይኖሩም፤መንፈሳቸው ተነሥቶ አይመጣም።አንተ ቀጣሃቸው፤ አጠፋሃቸው፤መታሰቢያቸውንም ሁሉ ደመሰስህ።
15. እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብን አበዛህ፤ሕዝብን አበዛህ።ክብሩን ለራስህ አደረግህ፤የምድሪቱንም ወሰን ሁሉ አሰፋህ።
16. እግዚአብሔር ሆይ፤ በተጨነቁ ጊዜ ወደ አንተ መጡ፤በገሠጽሃቸውም ጊዜ፣በለሆሳስ ድምፅ ይጸልያሉ።
17. እግዚአብሔር ሆይ፤ የፀነሰች ሴት ልትወልድ ስትል፣በምጥ እንደምትጨነቅና እንደምትጮኽ፣እኛም በፊትህ እንዲሁ ሆነናል።
18. አረገዝን በምጥም ተጨነቅን፤ነገር ግን ነፋስን ወለድን፤ለምድርም ድነትን አላመጣንም፤የዓለምን ሕዝብ አልወለድንም።