14. የሕዝቤን ቍስል እንደ ቀላል ቈጠሩ፣እንዲፈወስም ተገቢውን እንክብካቤ አላደረጉለትም፤ሰላምም ሳይኖር፣‘ሰላም፣ ሰላም’ ይላሉ።
15. ስለ ጸያፉ ተግባራቸው ዐፍረዋል እንዴ?ኧረ ጨርሶ ዕፍረት የላቸውም!ዕፍረት ምን እንደሆነ እንኳ አያውቁም፤ስለዚህ ከሚወድቁት ጋር ይወድቃሉ፤በምቀጣቸውም ጊዜ ይዋረዳሉ፤”ይላል እግዚአብሔር።
16. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“መንታ መንገድ ላይ ቁሙ፣ ተመልከቱም፤መልካሟን፣ የጥንቷን መንገድ ጠይቁ፤በእርሷም ላይ ሂዱ።ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ፤እናንተ ግን፣ ‘በእርሷ አንሄድም’ አላችሁ።
17. ጠባቂዎችን አቆምሁላችሁ፤‘የመለከትንም ድምፅ ስሙ’ አልኋችሁ፤እናንተ ግን፣ ‘አንሰማም’ አላችሁ።
18. እንግዲህ ሕዝቦች ሆይ ስሙ፤እናንተም ምስክሮች ምንእንደሚገጥማቸው አስተውሉ።
19. ምድር ሆይ፤ ስሚ፤ቃሌን ስላላደመጡ፣ሕጌንም ስለናቁ፣በዚህ ሕዝብ ላይ የሐሳባቸውን ውጤት፣ጥፋትን አመጣባቸዋለሁ።
20. ዕጣን ከሳባ ምድር፣ጣፋጩ ቅመም ከሩቅ አገር ቢመጣ ምን ይጠቅመኛል?የሚቃጠል መሥዋዕታችሁን አልቀበልም፤ሌላውም መሥዋዕታችሁ ደስ አያሰኙኝም፤
21. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤በዚህ ሕዝብ ፊት መሰናክልን አስቀምጣለሁ፤አባቶችና ወንዶች ልጆች በአንድነት ይደናቀፉበታል፤ጎረቤቶችና ባልንጀሮችም ይጠፋሉ።”
22. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ ሰራዊት፣ከሰሜን ምድር እየመጣ ነው፤ከምድር ዳርቻም፣ታላቅ ሕዝብ እየተነሣሣ ነው።
23. ቀስትና ጦር ይዘዋል፤ጨካኞችና ምሕረት የለሽ ናቸው፤ፈረሶቻቸውን ሲጋልቡ፤ድምፃቸው እንደተናወጠ ባሕር ነው፤የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ለሰልፍ የታጠቁ ሆነው፣ሊወጉሽ ይመጣሉ።”
24. ስለ እነርሱ ወሬ ደርሶናል፤ክንዶቻችንም ዝለዋል፤ጭንቀት ይዞናል፤ እንደምታምጥምሴት ሆነናል።
25. ጠላት ሰይፍ ታጥቆአል፤በየቦታውም ሽብር ሞልቶአል፤ስለዚህ ወደ ውጭ አትውጡ፤በየመንገዱ አትዘዋወሩ።
26. የሕዝቤ ልጅ ሆይ፤ ማቅ ልበሺ፤በዐመድም ላይ ተንከባለዪ፤አንድያ ልጁን እንዳጣ ሰው፣ምርር ብለሽ አልቅሺ፤አጥፊው በድንገት፣በላያችን ይመጣልና።
27. “ብረት እንደሚፈተን፣የሕዝቤን መንገድ፣አካሄዳቸውንም እንድትፈትን፣አንተን ፈታኝ አድርጌሃለሁ።
28. ሁሉም ለማማት የሚዞሩ፣ድድር ዐመፀኞች፣ናስና ብረት የሆኑ፣ምግባረ ብልሹዎች ናቸው።