ኢሳይያስ 44:15-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ሰው ለማገዶ ይጠቀምበታል፤ከዚያም ጥቂት ወስዶ በማንደድ ይሞቀዋል፤እንጀራም ይጋግርበታል።ከዚሁ ጠርቦ አምላክ ያበጃል፤ያመልከዋል፤ጣዖትን ይሠራል፤ ወድቆም ይሰግድለታል።

16. ግማሹን ዕንጨት ያነደዋል፤በላዩ ምግቡን ያበስልበታል፤ሥጋ ጠብሶበት እስኪጠግብ ይበላል፤እሳቱን እየሞቀ እንዲህ ይላል፤“እሰይ ሞቀኝ፤ እሳቱም ይታየኛል።”

17. በቀረው ዕንጨት የጣዖት አምላኩን ይሠራበታል፤ወድቆ ይሰግድለታል፤ ያመልከዋል፤ወደ እርሱም እየጸለየ፣“አንተ አምላኬ ነህ፤ አድነኝ” ይላል።

18. ምንም አያውቁም፤ አያስተውሉም፤እንዳያዩ ዐይናቸው ተሸፍኖአል፤እንዳያስተውሉ ልባቸው ተዘግቶአል።

19. ማንም ቆም ብሎ አላሰበም፤ዕውቀት ወይም ማስተዋል ስለሌለው እንዲህ ማለት አልቻለም፤“ግማሹን በእሳት አቃጥዬዋለሁ፤በፍሙ እንጀራ ጋግሬበታለሁ፤ሥጋ ጠብሼበት በልቻለሁ፤ታዲያ፣ በቀረው እንዴት ጸያፍ ነገር እሠራለሁ?ለግንድስ መስገድ ይገባኛልን?”

20. ዐመድ ይቅማል፤ ተታላይ ልብ አስቶታል፤ራሱን ለማዳን አይችልም፤“ይህ በቀኝ እጄ ያለው ነገር ሐሰት አይደለምን?”ለማለት አልቻለም።

21. “እስራኤል ሆይ፤ ባሪያዬ ነህና፣ያዕቆብ ሆይ፤ ይህን አስብ።እኔ ሠርቼሃለሁ፤ አንተም ባሪያዬ ነህ፤እስራኤል ሆይ፤ አልረሳህም።

22. መተላለፍህን እንደ ደመና፣ኀጢአትህን እንደ ማለዳ ጭጋግ ጠርጌ አስወግጃለሁ፤ተቤዥቼሃለሁናወደ እኔ ተመለስ።”

23. ሰማያት ሆይ፤ እግዚአብሔር ይህን አድርጎአልና ዘምሩ፤የምድር ጥልቆች ሆይ፤ በደስታ ጩኹ።እናንት ተራሮች፣እናንት ደኖችና ዛፎቻችሁ ሁሉ እልል በሉ፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአል፣በእስራኤልም ክብሩን ገልጦአልና።

24. “ከማሕፀን የሠራህ፣ የተቤዠህም፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ሁሉን ነገር የፈጠርሁ፣ብቻዬን ሰማያትን የዘረጋሁ፣ምድርን ያንጣለልሁ፣እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

25. የሐሰተኞችን ነቢያት ምልክቶች አከሽፋለሁ፤ሟርተኞችን አነሆልላለሁ፤የጥበበኞችን ጥበብ እገለባብጣለሁ፤ዕውቀታቸውንም ከንቱ አደርጋለሁ።

ኢሳይያስ 44