7. እርሱ ግን በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣“እኔ መፍትሔ አልሆንም፤በቤቴም ልብስና ምግብ የለኝም፤የሕዝብ መሪ አታድርጉኝ” ይላል።
8. ኢየሩሳሌም ተንገዳግዳለች፤ይሁዳም ለመውደቅ ተቃርባለች፤ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን የሚቃወም፣የክብሩንም መገኘት የሚያቃልል ነውና።
9. የፊታቸው ገጽታ ይመሰክርባቸዋል፤ኀጢአታቸውን እንደ ሰዶም በይፋ ይናገራሉ፤አይደብቁትምም፤ጥፋትን በራሳቸው ላይ ስላመጡ።ወዮላቸው!
10. ጻድቃን መልካም ነገር እንደሚያገኙ ንገሯቸው፤የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና።
11. በደለኞች ወዮላቸው፤ ጥፋትይመጣባቸዋል፤የእጃቸውን ያገኛሉና።
12. ወጣቶች ሕዝቤን ያስጨንቃሉ፤ሴቶችም ይገዟቸዋል።ሕዝቤ ሆይ፤ መሪዎችህ አሳስተውሃል፤ከመንገድህም መልሰውሃል።
13. እግዚአብሔር በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦአል፤በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተነሥቶአል።
14. እግዚአብሔር፣ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤“የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤
15. ሕዝቤን በችግር ስታደቁት፣የድኾችንም ፊት በሐዘን ስታገረጡት ምን ማለታችሁ ነው?”ይላል ጌታ፣የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
16. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤የጽዮን ሴቶች ኰርተዋል፤ዐንገታቸውን እያሰገጉ፣በዐይናቸውም እየጠቀሱ ይሄዳሉ፤እየተቈነኑ በመራመድ፣የእግራቸውን ዐልቦ ያቃጭላሉ።
17. ስለዚህ፣ ጌታ በጽዮን ሴቶች ዐናት ላይቈረቈር ያመጣል፤ እግዚአብሔርም ራሳቸውን ቡሀ ያደርጋል።
18. በዚያም ቀን ጌታ የክብር ጌጣቸውን ይነጥቃቸዋል፤ የእግር አንባሩን፣ የጠጒር ጌጡን፣ የጨረቃ ቅርጽ ያለውን የዐንገት ጌጥ፣
19. የጆሮ ጒትቻውን፣ የእጅ አንባሩን፣ የፊት መሸፈኛውን፣
20. የራስ መሸፈኛውን፣ ዐልቦውን፣ ሻሹን፣ የሽቶ ብልቃጡን፣ አሸንክታቡን፣
21. የጣት ቀለበቶችንና የአፍንጫ ቀለበቶችን፣
22. ያማረውን ቀሚስ፣ የውስጥ ልብሱን፣ ካባውን፣ የእጅ ቦርሳውን፣
23. መስታወቱን፣ ከጥሩ በፍታ የተሠራውን ልብስ፣ የራስ ጌጡን፣ ዐይነ ርግቡን ሁሉ ይነጥቃቸዋል።
24. በሽቶ ፈንታ ግማት፣በሻሽ ፈንታ ገመድ፣አምሮ በተሠራ ጠጒር ፈንታ ቡሀነት፣ባማረ ልብስ ፈንታ ማቅ፣በውበትም ፈንታ ጠባሳ ይሆናል።