ኤርምያስ 6:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. በምድሪቱ በሚኖሩት ላይ፣እጄን በምዘረጋበት ጊዜ፣ዕርሻቸውና ሚስቶቻቸው ሳይቀሩ፣ቤቶቻቸው ለሌሎች ይሆናሉ፤”ይላል እግዚአብሔር።

13. “ከትንሹ እስከ ትልቁ ሰው፣ሁሉም ለጥቅም የሚስገበገቡ ናቸው፤ነቢያቱም ካህናቱም ሳይቀሩ፣ሁሉም ያጭበረብራሉ።

14. የሕዝቤን ቍስል እንደ ቀላል ቈጠሩ፣እንዲፈወስም ተገቢውን እንክብካቤ አላደረጉለትም፤ሰላምም ሳይኖር፣‘ሰላም፣ ሰላም’ ይላሉ።

15. ስለ ጸያፉ ተግባራቸው ዐፍረዋል እንዴ?ኧረ ጨርሶ ዕፍረት የላቸውም!ዕፍረት ምን እንደሆነ እንኳ አያውቁም፤ስለዚህ ከሚወድቁት ጋር ይወድቃሉ፤በምቀጣቸውም ጊዜ ይዋረዳሉ፤”ይላል እግዚአብሔር።

16. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“መንታ መንገድ ላይ ቁሙ፣ ተመልከቱም፤መልካሟን፣ የጥንቷን መንገድ ጠይቁ፤በእርሷም ላይ ሂዱ።ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ፤እናንተ ግን፣ ‘በእርሷ አንሄድም’ አላችሁ።

17. ጠባቂዎችን አቆምሁላችሁ፤‘የመለከትንም ድምፅ ስሙ’ አልኋችሁ፤እናንተ ግን፣ ‘አንሰማም’ አላችሁ።

18. እንግዲህ ሕዝቦች ሆይ ስሙ፤እናንተም ምስክሮች ምንእንደሚገጥማቸው አስተውሉ።

19. ምድር ሆይ፤ ስሚ፤ቃሌን ስላላደመጡ፣ሕጌንም ስለናቁ፣በዚህ ሕዝብ ላይ የሐሳባቸውን ውጤት፣ጥፋትን አመጣባቸዋለሁ።

20. ዕጣን ከሳባ ምድር፣ጣፋጩ ቅመም ከሩቅ አገር ቢመጣ ምን ይጠቅመኛል?የሚቃጠል መሥዋዕታችሁን አልቀበልም፤ሌላውም መሥዋዕታችሁ ደስ አያሰኙኝም፤

21. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤በዚህ ሕዝብ ፊት መሰናክልን አስቀምጣለሁ፤አባቶችና ወንዶች ልጆች በአንድነት ይደናቀፉበታል፤ጎረቤቶችና ባልንጀሮችም ይጠፋሉ።”

ኤርምያስ 6