ኢሳይያስ 48:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “የያዕቆብ ቤት ሆይ፤እናንት በእስራኤል ስም የተጠራችሁ፣ከይሁዳ ዘር የተገኛችሁ፣እናንት በእግዚአብሔር ስም የምትምሉ፣በእውነት ወይም በጽድቅ ሳይሆን፣የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ ይህን ስሙ!

2. እናንት የቅድስቲቱ ከተማ ነዋሪዎች ነን ብላችሁ ራሳችሁን የምትጠሩ፣በእስራኤል አምላክ የምትታመኑ፣ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው የሚለውን አድምጡ፤

3. የቀደሙትን ነገሮች ከብዙ ዘመን በፊት ተናግሬአለሁ፤ከአፌ ወጥተዋል፤ እንዲታወቁም አድርጌአለሁ፤እኔም ድንገት ሠራሁ እነርሱም፤ ተፈጸሙ።

4. የቱን ያህል እልኸኛ እንደ ነበርህ ዐውቃለሁና፤የዐንገትህ ጅማት ብረት፣ግንባርህም ናስ ነበር።

5. ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ገና ድሮ ነገርሁህ፤ከመፈጸማቸው በፊት አስታወቅሁህ፤ ይህም፣‘ጣዖቶቼ ይህን አደረጉ፤ከዕንጨት የተቀረጸው ምስልና ከብረት የተሠራው አምላኬ ይህን ወስኖአል’እንዳትል ነው።

6. እነዚህን ነገሮች ሰምተሃል፤ ሁሉንም ተመልከታቸው፤ራስህ ትክክለኛነታቸውን አትመሰክርምን?“ከአሁን ጀምሮ አዳዲስ ነገሮችን፣የተሰወሩብህን ያላወቅሃቸውን ነገሮች እነግርሃለሁ።

7. እነርሱም የተፈጠሩት አሁን እንጂ ጥንት አይደለም፤ስለ እነርሱም ከዛሬ በፊት አልሰማህም።ስለዚህ፣ ‘አዎን፤ ስለ እነርሱ ዐውቃለሁ’ማለት አትችልም።

8. አልሰማህም ወይም አላውቅህም፤ጆሮህ ከጥንት የተከፈተ አልነበረም፤አንተ አታላይ እንደ ነበርህ፣ከልጅነትህ ጀምሮ ዐመፀኛ መባልህን ዐውቄአለሁና።

9. ስለ ስሜ ስል ቍጣዬን አዘገያለሁ፤ስለ ምስጋናዬም ስል ከአንተ እገታዋለሁ፤ይኸውም እንዳልቈርጥህ ነው።

ኢሳይያስ 48