1. ቤል ተዋረደ፤ ናባው እጅግ ዝቅ አለ፤ጣዖቶቻቸው በአጋሰስ ተጭነዋል፤ይዘዋቸው የሚዞሩት ምስሎች ሸክም ናቸው፤ለደከሙ እንስሳት ከባድ ጭነት ናቸው።
2. እነርሱም በአንድ ላይ ዝቅ ይላሉ፤ ያጐነብሳሉ፤ጭነቱን ለማዳን አይችሉም፤ራሳቸውም በምርኮ ይወሰዳሉ።
3. “እናንት የያዕቆብ ቤት ሆይ፤የእስራኤል ቤት ቅሬታ ሁሉ፣ከተፀነሳችሁበት ጊዜ ጀምሮ የያዝኋችሁ፣ከተወለዳችሁበት ጊዜ ጀምሮ የተሸከምኋችሁ ስሙኝ።
4. እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ።ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ።
5. “ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ? ከማንስ ጋር እኩል ታደርጉኛላችሁ?እንመሳሰልስ ዘንድ ከማን ጋር ታነጻጽሩኛላችሁ?
6. ሰዎች ወርቅ ከከረጢታቸው ይዘረግፋሉ፤ብርንም በሚዛን ይመዝናሉ፤አንጥረኛን ይቀጥራሉ፤ እርሱም አምላክ አድርጎ ያበጅላቸዋል።እነርሱም ይሰግዱለታል፤ ያመልኩታልም።
7. አንሥተው በትከሻቸው ይሸከሙታል፤እቦታው ያደርጉታል፤ በዚያም ይቆማል፤ከዚያም ቦታ አይንቀሳቀስም፤ማንም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይመልስም፤ከጭንቅቱም አያድነውም።