ኢሳይያስ 28:13-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል፣በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፤በደንብ ላይ ደንብ፣ በደንብ ላይ ደንብ፤እዚህ ጥቂት እዚያ ጥቂት ይሆንባቸዋል።ይህ የሚሆንባቸው ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፣እንዲቈስሉና በወጥመድ እንዲያዙ፣እንዲማረኩም ነው።

14. ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ፣እናንት ፌዘኞች የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

15. እናንት፣ “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል፤ከሲኦልም ጋር ስምምነት አድርገናል፤ውሸትን መጠጊያችን፣ሐሰትን መደበቂያችን አድርገናል፤ታላቅ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣ሊነካን አይችልም” በማለት ታብያችኋል።

16. ስለዚህ ልዑል እግዚእብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ የተፈተነ ድንጋይ፣ የመሠረት ድንጋይ፣ለጽኑ መሠረት የሚሆን የከበረ የማእዘን ድንጋይ፣በጽዮን አስቀምጣለሁ፤በእርሱም የሚያምን አያፍርም።

17. ፍትሕን የመለኪያ ገመድ፣ጽድቅንም ቱንቢ አደርጋለሁ፤ውሸት መጠጊያችሁን የበረዶ ዝናብ ይጠራርገዋልመደበቂያችሁንም ውሃ ያጥለቀልቀዋል።

18. ከሞት ጋር የገባችሁት ቃል ኪዳን ይሻራል፤ከሲኦልም ጋር ያደረጋችሁት ስምምነት ይፈርሳል፤ታላቁ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣እናንተም ትጠራረጋላችሁ።

19. በመጣ ቍጥር ይዞአችሁ ይሄዳል፤ማለዳ ማለዳ፣ በቀንና በሌሊትምይጠራርጋል።”ይህን ቃል ብታስተውሉ፣ሽብር በሽብር በሆነ ነበር።

20. እግር ዘርግቶ እንዳይተኛ ዐልጋው አጭር ነው፤ሰውነትንም ለመሸፋፈን ብርድ ልብሱ ጠባብ ነው።

21. እግዚአብሔር ሥራውን፣ አዎን ድንቅ ሥራውን ሊሠራ፣ተግባሩን፣ እንግዳ የሆነ ተግባሩን ሊያከናውን፣በፐራሲም ተራራ እንዳደረገው ይነሣል፣በገባዖን ሸለቆ እንዳደረገው ይነሣሣል።

22. እንግዲህ ፌዛችሁን አቁሙ፤አለዚያ እስራታችሁ ይጸናባችኋል፤ጌታ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣መላውን ምድር ለማጥፋት ያወጀውን ዐዋጅ ሰምቻለሁ።

23. አድምጡ ድምፄን ስሙ፤አስተውሉ ቃሌንም ስሙ።

24. ገበሬ ሊዘራ መሬቱን ሲያዘጋጅ ያለ ማቋረጥ ያርሳልን?ጓሉን ሲከሰክስ፣ ዐፈሩን ሲያለሰልስ ይከርማልን?

25. ዕርሻውን አስተካክሎ፣ጥቍር አዝሙድና ከሙን አይዘራምን?ስንዴውንስ በትልሙ፣ገብሱን በተገቢ ቦታው፣አጃውንም በተመደበው ስፍራ አይዘራምን?

26. አምላኩ ያስተምረዋል፤ትክክለኛውንም መንገድ ያሳየዋል።

27. ጥቍር አዝሙድ በመውቂያ መሣሪያ አይወቃም፤ከሙን የሠረገላ መንኰራኵር አይሄድበትም፤ጥቍር አዝሙድ በበትር፣ከሙንም በዘንግ ይወቃል።

28. እንጀራን ለመጋገር እህል ይፈጫል፤ስለዚህ አንድ ሰው ለዘላለም እህል ሲወቃ አይኖርም።የመውቂያውን መንኰራኵር ቢያኼድበትም፣ፈረሶቹ አይደፈጥጡትም።

29. ይህ ሁሉ የሚሆነው በምክሩ ድንቅ በጥበቡታላቅ ከሆነው፣ከሰራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

ኢሳይያስ 28