1. ስለ ታረዱት ወገኖቼ፣ቀንና ሌሊት አለቅስ ዘንድ፣ምነው፣ ራሴ የውሃ ምንጭ በሆነ!ምነው ዐይኖቼ የእንባ መጒረፊያ በሆኑልኝ!
2. ሕዝቤን ትቼ፣ ርቄ እንድሄድ፣በምድረ በዳ የእንግዶች ማደሪያ ማን በሰጠኝ!ሁሉም አመንዝሮች፣የአታላዮች መንጋ ሆነዋላ!
3. “ሐሰትን ለመናገር፣ምላሳቸውን እንደ ቀስት ገተሩ፤በእውነት ሳይሆን፣በሐሰት በምድሪቱ ገነኑ፤ከክፋት ወደ ክፋት ሄዱ፤እኔንም አላወቁኝም፤”ይላል እግዚአብሔር።
4. “እያንዳንዱ ወንድም አታላይ፣ባልንጀራም ሁሉ ሐሜተኛ ስለ ሆነ፣ወንድም ከወንድሙ፣ ይጠንቀቅ፣ባልንጀራም በጓደኛው አይታመን።
5. ባልንጀራ ባልንጀራውን ያታልላል፤እውነትን የሚናገር የለም፤ሐሰትን ይናገር ዘንድ ምላሳቸውን አሠልጥነዋል፤ኀጢአትንም በማድረግ ራሳቸውን አድክመዋል።
6. መኖሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፤ከሽንገላቸውም የተነሣ ሊያውቁኝ አልፈቀዱም፤”ይላል እግዚአብሔር።
7. ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ እንደ ብረት አነጥራቸዋለሁ፤ እፈትናቸዋለሁም፤ስለ ሕዝቤ ኀጢአት፣ከዚህ የተለየ ምን ማድረግ እችላለሁ?
8. ምላሳቸው የሚገድል ቀስት ነው፤በሽንገላ ይናገራል፤ሁሉም ከባልንጀራው ጋር በፍቅር ይናገራል፤በልቡ ግን ያደባበታል።
9. ታዲያ ስለ እነዚህ ነገሮች ልቀጣቸው አይገባኝምን?”ይላል እግዚአብሔር፤“እንደዚህ ዐይነቱንስ ሕዝብ፣አልበቀልምን?
10. ስለ ተራሮች አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይ እላለሁ፤በምድረ በዳ ስላሉትም መሰማሪያዎች አዝናለሁ፤ሰው የማያልፍባቸው ባድማ ሆነዋል፤የከብቶች ጩኸት አይሰማም፤የሰማይ ወፎች ሸሽተዋል፤የዱር አራዊትም ጠፍተዋል።
11. “ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር፣የቀበሮም ጐሬ አደርጋታለሁ፤የይሁዳንም ከተሞች፣ሰው የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ።”
12. ይህን መረዳት የሚችል ጥበበኛ ሰው ማን ነው? እግዚአብሔር ገልጾለት ይህንስ ማስረዳት የሚችል ማን ነው? ምድሪቱስ ሰው እንደማያልፍበት በረሓ ለምን ጠፋች? ለምን ወና ሆነች?
13. እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ይህ የሆነው የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተው ስላልታዘዙኝና ሥርዐቴን ስላልተከተሉ ነው።
14. በዚህ ፈንታ፣ በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ አባቶቻቸው ያስተማሯቸውን በአሊምን ተከተሉ።”
15. ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ይህን ሕዝብ መራራ ምግብ አበላዋለሁ፤ የተመረዘንም ውሃ አጠጣዋለሁ።