መክብብ 12:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣“ደስ አያሰኙኝም”የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፣በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ።

2. ፀሓይና ብርሃን፣ጨረቃና ከዋክብት ሳይጨልሙ፣ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፣

3. ቤት ጠባቂዎች ሲርዱ፣ብርቱዎች ሲጐብጡ፣ጥቂት በመሆናቸው ፈጪታዎች ሲያቆሙ፣በመስኮት የሚያዩትም ሲፈዙ፣

4. ወደ አደባባይ የሚያወጡ በሮች ሲዘጉ፣ወፍጮ ሟልጦ ድምፁ ሲላሽ፣ሰው በወፍ ድምፅ ሲነሣ፣ዝማሬው ሁሉ ሲዳከም፤

5. ዳገት መውጣት ሲያርድ፣መንገድም ሲያስፈራ፣የለውዝ ዛፍ ሲያብብ፣አንበጣም ራሱን ሲጐትት፣ፍላጎት ሲጠፋ፤በዚያም ጊዜ ሰው ወደ ዘላለማዊ ቤቱ ይሄዳል፤አልቃሾችም በአደባባዮች ይዞራሉ።

6. የብር ሰንሰለት ሳይበጠስ፣የወርቅ ሳሕንም ሳይሰበር፣የውሃ መቅጃው በምንጩ አጠገብ ሳይከሰከስ፣ወይም መንኰራኵሩ በውሃ ጒድጓድ ላይ ሳይሰበር፣

7. ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ፣መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ፣ፈጣሪህን አስብ።

መክብብ 12