ዘፍጥረት 49:12-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ዐይኖቹ ከወይን ጠጅ የቀሉ፣ጥርሶቹም ከወተት ይልቅ የነጡ ይሆናሉ።

13. “ዛብሎን፣ በባሕር ዳር ይኖራል፤የመርከቦች መጠጊያም ይሆናል፤ወሰኑም እስከ ሲዶና ይደርሳል።

14. “ይሳኮር፣ ዐጥንተ ብርቱ አህያ፣በጭነት መካከል የሚተኛ፣

15. ማረፊያ ቦታው መልካም፣ምድሪቱም አስደሳች መሆኗን ሲያይ፣ትከሻውን ለሸክም ያመቻቻል፤ተገድዶም ያገለግላል።

16. “ዳን፣ ከእስራኤል ነገዶች እንደ አንዱ ሆኖ፣በራሱ ሕዝብ ላይ ይፈርዳል።

17. ዳን የመንገድ ዳር እባብ፣የመተላለፊያም መንገድ እፉኝት ነው፤ጋላቢው የኋሊት እንዲወድቅ፣የፈረሱን ሰኮና ይነክሳል።

18. “እግዚአብሔር ሆይ (ያህዌ)፤ ማዳንህን እጠባበቃለሁ።

19. “ጋድን ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፤እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል።

20. “አሴር ማእደ ሰፊ ይሆናል፤ለነገሥታትም የሚስማማ ምግብ ያቀርባል።

21. “ንፍታሌም ነጻ እንደ ተለቀቀች፣የሚያማምሩም ግልገሎችእንደምትወልድ ሚዳቋ ነው።

22. ዮሴፍ፤ ፍሬያማ የወይን ተክል፣በምንጭ ዳር የተተከለ ወይን ነው።ሐረጎቹ ቅጥርን ያለብሳሉ።

23. ቀስተኞች በጭካኔ አጠቁት፤በጥላቻም ነደፉት።

24. ነገር ግን በያዕቆብ ኀያል አምላክ ክንድ፣እረኛው በሆነው በእስራኤል ዐለት፣ ቀስቱ ጸና፤ጠንካራ ክንዱም ቀለጠፈ።

25. አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣በሚባርክህ፣ ሁሉን ማድረግ በሚችል አምላክ፣ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣ከማሕፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል።

26. ከጥንት ተራሮች በረከት፣ከዘላለም ኰረብቶች ምርቃት ይልቅ፣የአባትህ በረከት ይበልጣል፤ይኸ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ ይውረድ፤በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ግንባር ላይ ይረፍ።

27. ብንያም፣ ነጣቂ ተኵላ ነው፤ያደነውን ማለዳ ይበላል፤የማረከውን ማታ ይከፋፈላል።

ዘፍጥረት 49