ኤርምያስ 6:4-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. “በእርሷ ላይ ጦርነት ዐውጁ፤ተነሡ በቀትር አደጋ እንጣልባት፤ወይ ጉድ! ቀኑ እኮ መሸብን!ጥላው ረዘመ።

5. እንግዲህ ተነሡ በሌሊት እናጥቃት፤ምሽጎቿንም እንደምስስ!”

6. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ዛፎቹን ቍረጡ፤በኢየሩሳሌም ዙሪያ የዐፈር ድልድል ሥሩ።ይህቺ ከተማ ቅጣት ይገባታል፤ግፍን ተሞልታለችና።

7. የውሃ ጒድጓድ ውሃ እንደሚያመነጭ፣እርሷም እንዲሁ ክፋቷን ታፈልቃለች።ዐመፅና ጥፋት በውስጧ ይስተጋባል፤ሕመሟና ቍስሏ ዘወትር ይታየኛል።

8. ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተጠንቀቂ፤አለበለዚያ ከአንቺ ዘወር እላለሁ፤ማንም ሊኖርባት እስከማይችል ድረስ፣ምድርሽን ባዶ አደርጋለሁ።”

9. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የወይን ፍሬ ተሟጦ እንደሚቃረም፣ከእስራኤል የተረፉትን እንዲሁ ይቃርሟቸው።ወይን ለቃሚ እንደሚለቅም፣እጅህን ወደ ቅርንጫፎቹ ደጋግመህ ዘርጋ።”

10. ለማን ልናገር? ማንን ላስጠንቅቅ?ማንስ ይሰማኛል?እነሆ፣ ጆሮዎቻቸው አልተገረዙምና፣መስማት አይችሉም። በእግዚአብሔር ቃል ይሣለቃሉ፤ደስም አይሰኙበትም።

11. በእነርሱ ላይ በእግዚአብሔር ቍጣ ተሞልቻለሁ፤በውስጤም ልይዘው አልቻልሁም።“መንገድ ላይ በሚገኙ ሕፃናት፣በተሰበሰቡ ወጣቶችም ላይ አፍስሰው፤ባልም ሚስትም፣ያረጁና የጃጁም አያመልጡም።

12. በምድሪቱ በሚኖሩት ላይ፣እጄን በምዘረጋበት ጊዜ፣ዕርሻቸውና ሚስቶቻቸው ሳይቀሩ፣ቤቶቻቸው ለሌሎች ይሆናሉ፤”ይላል እግዚአብሔር።

13. “ከትንሹ እስከ ትልቁ ሰው፣ሁሉም ለጥቅም የሚስገበገቡ ናቸው፤ነቢያቱም ካህናቱም ሳይቀሩ፣ሁሉም ያጭበረብራሉ።

14. የሕዝቤን ቍስል እንደ ቀላል ቈጠሩ፣እንዲፈወስም ተገቢውን እንክብካቤ አላደረጉለትም፤ሰላምም ሳይኖር፣‘ሰላም፣ ሰላም’ ይላሉ።

15. ስለ ጸያፉ ተግባራቸው ዐፍረዋል እንዴ?ኧረ ጨርሶ ዕፍረት የላቸውም!ዕፍረት ምን እንደሆነ እንኳ አያውቁም፤ስለዚህ ከሚወድቁት ጋር ይወድቃሉ፤በምቀጣቸውም ጊዜ ይዋረዳሉ፤”ይላል እግዚአብሔር።

16. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“መንታ መንገድ ላይ ቁሙ፣ ተመልከቱም፤መልካሟን፣ የጥንቷን መንገድ ጠይቁ፤በእርሷም ላይ ሂዱ።ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ፤እናንተ ግን፣ ‘በእርሷ አንሄድም’ አላችሁ።

17. ጠባቂዎችን አቆምሁላችሁ፤‘የመለከትንም ድምፅ ስሙ’ አልኋችሁ፤እናንተ ግን፣ ‘አንሰማም’ አላችሁ።

ኤርምያስ 6