1. “እናንት የብንያም ልጆች፤ ክፉ ነገር፣ታላቅም ጥፋት ከሰሜን ድንገት ይመጣልና፣ከኢየሩሳሌም ሸሽታችሁ አምልጡ፤በቴቁሔ መለከትን ንፉ፤በቤትሐካሪም ላይ ምልክት ከፍአድርጋችሁ አሳዩ።
2. ውብና ሽሙንሙን የሆነችዋን፣የጽዮንን ሴት ልጅ አጠፋታለሁ።
3. እረኞች መንጎቻቸውን ይዘው ይመጡባታል፤ድንኳናቸውን በዙሪያዋ ይተክላሉ፤እያንዳንዳቸውም በየአቅጣጫቸው መንጋቸውን ያሰማራሉ።”
4. “በእርሷ ላይ ጦርነት ዐውጁ፤ተነሡ በቀትር አደጋ እንጣልባት፤ወይ ጉድ! ቀኑ እኮ መሸብን!ጥላው ረዘመ።
5. እንግዲህ ተነሡ በሌሊት እናጥቃት፤ምሽጎቿንም እንደምስስ!”
6. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ዛፎቹን ቍረጡ፤በኢየሩሳሌም ዙሪያ የዐፈር ድልድል ሥሩ።ይህቺ ከተማ ቅጣት ይገባታል፤ግፍን ተሞልታለችና።
7. የውሃ ጒድጓድ ውሃ እንደሚያመነጭ፣እርሷም እንዲሁ ክፋቷን ታፈልቃለች።ዐመፅና ጥፋት በውስጧ ይስተጋባል፤ሕመሟና ቍስሏ ዘወትር ይታየኛል።
8. ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተጠንቀቂ፤አለበለዚያ ከአንቺ ዘወር እላለሁ፤ማንም ሊኖርባት እስከማይችል ድረስ፣ምድርሽን ባዶ አደርጋለሁ።”