15. ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ነቢያት እንዲህ ይላል፤“ከኢየሩሳሌም ነቢያት፣በምድሪቱ ሁሉ ርኵሰት ተሠራጭቶአልና፤መራራ ምግብ አበላቸዋለሁ፤የተመረዘም ውሃ አጠጣቸዋለሁ።”
16. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነዚህ ነቢያት የሚተነብዩላችሁን አትስሙ፤በባዶ ተስፋ ይሞሏችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ሳይሆን፣ከገዛ ልባቸው የሆነውን ራእይ ይናገራሉ።
17. እኔን ለሚንቁኝ፣‘እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል’ ይላሉ፤የልባቸውን እልኸኝነት ለሚከተሉም ሁሉ፣‘ክፉ ነገር አይነካችሁም’ ይሏቸዋል።
18. ቃሉን ለማየትና ለመስማት፣እነማን የእግዚአብሔር ምክር ባለበት ቆመዋል?ቃሉን ያደመጠ፣ የሰማስ ማን ነው?
19. እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፣በቍጣ ይነሣል፤ብርቱም ማዕበል፣የክፉዎችን ራስ ይመታል።
20. እግዚአብሔር የልቡን ሐሳብ፣ሙሉ በሙሉ ሳይፈጽም፣ቍጣው እንዲሁ አይመለስም፤በኋለኛው ዘመን፣ይህን በግልጽ ትረዳላችሁ።
21. እኔ እነዚህን ነቢያት አልላክኋቸውም፤እነርሱ ግን ለራሳቸው መልእክታቸውን ይዘው ሮጡ፣ሳልናገራቸውም፣ትንቢት ተናገሩ።
22. ምክሬ ባለበት ቢቆሙ ኖሮ፣ቃሌን ለሕዝቤ ባሰሙ ነበር፤ከክፉ መንገዳቸው፣ከክፉ ሥራቸውም በመለሷቸው ነበር።
23. “እኔ የቅርብ አምላክ ብቻ ነኝን?ይላል እግዚአብሔር፤“የሩቅስ አምላክ አይደለሁምን?
24. እኔ እንዳላየው፣በስውር ቦታ ሊሸሸግ የሚችል አለን?”ይላል እግዚአብሔር።“ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን”ይላል እግዚአብሔር።