ኤርምያስ 10:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔር የሚላችሁን ስሙ።

2. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የአሕዛብን መንገድ አትከተሉ፤እነርሱ በሰማይ ምልክቶች ይታወካሉ፣እናንተ ግን በእነዚህ አትረበሹ።

3. የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ዛፍ ከጫካ ይቈርጣሉ፤አናጺም በመሣሪያው ቅርጽ ያበጅለታል፤

4. በብርና በወርቅ ይለብጡታል፤እንዳይወድቅም፣በመዶሻ መትተው በምስማር ያጣብቁታል።

5. ጣዖቶቻቸው በዱባ ዕርሻ መካከል እንደ ቆመ ማስፈራርቾ ናቸው፤የመናገር ችሎታ የላቸውም፤መራመድም ስለማይችሉ፣ተሸካሚ ያስፈልጋቸዋል፤ጒዳት ማድረስም ሆነ፣መልካምን ነገር ማድረግ ስለማይችሉ፣አትፍሯቸው።”

6. እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዳንተ ያለ ማንም የለም፤አንተ ታላቅ ነህ፤የስምህም ሥልጣን ታላቅ ነው።

7. የሕዝቦች ሁሉ ንጉሥ ሆይ፤አንተን የማይፈራ ማነው?ክብር ይገባሃልና።ከምድር ጠቢባን ሁሉ፣ከመንግሥቶቻቸውም ሁሉ መካከል፣እንዳንተ ያለ የለም።

8. ከከንቱ የዕንጨት ጣዖት ትምህርት የሚቀስሙ ሁሉ፣ጅሎችና ሞኞች ናቸው።

9. የተጠፈጠፈ ብር ከተርሴስ፣ወርቅም ከአፌዝ ይመጣል።ባለሙያውና አንጥረኛው የሠሯቸው፣ብልኀተኞችም ያበጇቸው ሁሉ፣ሰማያዊና ሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፈዋል።

10. እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም ንጉሥ ነው፤በሚቈጣበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤መንግሥታትም ቍጣውን ሊቋቋሙ አይችሉም።

11. “እናንተም፣ ‘እነዚህ ሰማያትንና ምድርን ያልፈጠሩ አማልክት ከምድር ላይ፣ ከሰማያትም በታች ይጠፋሉ’ ትሏቸዋላችሁ።”

ኤርምያስ 10