ኢሳይያስ 62:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ጽድቋ እንደ ማለዳ ወጋገን እስኪፈነጥቅ፣ድነቷ እንደሚያንጸባርቅ ፋና እስኪታይ፣ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም።

2. መንግሥታት ጽድቅሽን፣ነገሥታት ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔር አፍ በሚያወጣልሽ፣በአዲስ ስም ትጠሪያለሽ።

3. በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፣በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።

4. ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤ነገር ግን፣ “ደስታዬ በእርሷ” ትባያለሽ፤ምድርሽም፣ “ባለ ባል” ትባላለች፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ምድርሽም ባለ ባል ትሆናለች።

5. ጐልማሳ ድንግሊቱን እንደሚያገባ፣ልጆችሽ እንዲሁ ያገቡሻል፤ሙሽራ በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፣አምላክሽም በአንቺ ደስ ይለዋል።

6. ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ዘብ ጠባቂዎችን በቅጥሮችሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ቀንም ሆነ ሌሊት ፈጽሞ አይታክቱም።እናንት ወደ እግዚአብሔር አቤት፣ አቤት የምትሉ፤ፈጽሞ አትረፉ፤

7. ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት፣የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ዕረፍት አትስጡት።

ኢሳይያስ 62