1. በዚያ ቀን ይህ መዝሙር በይሁዳ ምድር ይዘመራል፤ብርቱ ከተማ አለችን፣አምላካችን ቅጥሮቿንና ምሽጎቿን፣ለድነት አድርጎአል።
2. በእምነቱ የጸናጻድቅ የሆነ ሕዝብ ይገባ ዘንድ፣በሮቿን ክፈቱ።
3. በአንተ ላይ ታምናለችና፣በአንተ የምትደገፈውን ነፍስፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።
4. በእግዚአብሔር ለዘላለም ታመኑ፤ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም ዐምባ ነውና።
5. በከፍታ የሚኖሩትን ዝቅ ዝቅ ያደርጋል፤ከፍ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፤ወደ ምድር ይጥላታል፤ከትቢያም ጋር ይደባልቃታል።
6. እግር፣የተጨቋኞች እግር፣የድኾች ኮቴ ይረግጣታል።
7. የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤አንተ ቅን የሆንህ ሆይ፤የጻድቃንን መንገድ ታቃናለህ።
8. እግዚአብሔር ሆይ፤ በሕግህ ጐዳና በመሄድ፣አንተን ተስፋ አድርገናል፤ስምህና ዝናህ፣የልባችን ምኞት ነው።