1. እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድርን ባድማ ያደርጋታል፤ፈጽሞ ያጠፋታል፤የፍርስራሽ ክምር ያደርጋታል፤ነዋሪዎቿንም ይበትናል።
2. ነገሩ ሁሉም አንድ ዐይነት ይሆናል፤በሕዝቡ ላይ የሚሆነው በካህኑ፣በአገልጋዩ ላይ የሚሆነው በጌታው፣በአገልጋይዋ ላይ የሚሆነው በእመቤቷ፣በገዢው ላይ የሚሆነው በሻጩ፣በተበዳሪው ላይ የሚሆነው በአበዳሪው፣በብድር ከፋይ ላይ የሚሆነው በብድር ሰጪው ይሆናል።
3. ምድር ፈጽሞ ባድማ ትሆናለች፤ጨርሶም ትበዘበዛለች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና።
4. ምድር ትደርቃለች፤ ትረግፋለች፤ዓለም ትዝላለች፤ ትረግፋለች፤የምድርም መሳፍንት ይዝላሉ።
5. ምድር በሕዝቧ ትረክሳለች፤ሕግን ጥሰዋል፤ሥርዐትን ተላልፈዋል፤ዘላለማዊውንም ኪዳን አፍርሰዋል።