ሕዝቅኤል 30:11-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ከአሕዛብ ሁሉ እጅግ ጨካኝ የሆኑት፣ እርሱና ሰራዊቱ፣ምድሪቱን ለማጥፋት እንዲመጡ ይደረጋል፤ሰይፋቸውን በግብፅ ላይ ይመዛሉ፤ምድሪቱንም ሬሳ በሬሳ ያደርጋሉ፤

12. የዐባይን ወንዝ ውሃ አደርቃለሁ፤ምድሪቱን ለክፉ ሰዎች እሸጣለሁ፤በባዕዳን እጅ፣ ምድሪቷንና በውስጧያለውን ሁሉ ባድማ አደርጋለሁ፤እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።

13. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ጣዖታትን አጠፋለሁ፤በሜምፊስ ያሉትን ምስሎች እደመስሳለሁ።ከእንግዲህ በግብፅ ገዥ አይኖርም፣በምድሪቱም ላይ ፍርሀት እሰዳለሁ።

14. ጳፕሮስን ባድማ አደርጋለሁ፤በጣኔዎስ ላይ እሳት እለኵሳለሁ፤በቴብስ ላይ ቅጣት አመጣለሁ።

15. የግብፅ ምሽግ በሆነችው፣በሲን ላይ መዓቴን አፈሳለሁ፤ስፍር ቍጥር የሌለውን የቴብስን ሕዝብ አጠፋለሁ።

16. በግብፅ ላይ እሳት አነዳለሁ፤ሲን በጭንቅ ትናጣለች፤ቴብስ በማዕበል ትወሰዳለች፤ሜምፊስ በማያቋርጥ ጭንቀት ውስጥ ትገባለች።

17. የሄልዮቱና የቡባስቱ ጐልማሶች፣በሰይፍ ይወድቃሉ፤ከተሞቹ ራሳቸውም ይማረካሉ።

18. የግብፅን ቀንበር በምሰብርበት ጊዜ፣በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል፤ከዚያም የተኵራራችበት ብርታት ይንኰታኰታል።በደመና ትሸፈናለች፤መንደሮቿም ይማረካሉ።

19. ስለዚህ በግብፅ ላይ ቅጣቴን አመጣለሁ፤እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

20. በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር በሰባተኛው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

21. “የሰው ልጅ ሆይ፤ የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬአለሁ፤ ይፈወስ ዘንድ ክንዱ አልተጠገነም፤ ወይም ሰይፍ መያዝ ይችል ዘንድ እጁ በመቃ አልታሰረም።

22. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ተነሥቻለሁ፤ ደኅናውንና የተሰበረውን፣ ሁለቱንም ክንዶቹን እሰብራለሁ፤ ሰይፉም ከእጁ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።

23. ግብፃውያንን በሕዝቦች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ።

ሕዝቅኤል 30