ዘፍጥረት 35:9-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለያዕቆብ ዳግመኛ ተገለጠለት፤ ባረከውም።

10. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “እስካሁን ስምህ ያዕቆብ ነበረ፤ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ነገር ግን ስምህ እስራኤል ይባላል” አለው።ስለዚህም እስራኤል ብሎ ጠራው።

11. ደግሞም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ነኝ፤ ብዛ ተባዛ፤ ሕዝብና የሕዝቦች ማኅበር ከአንተ ይወጣሉ፤ ነገሥታትም ከአብራክህ ይከፈላሉ።

12. ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ከአንተም በኋላ ይህችኑ ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።”

13. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።

14. ያዕቆብ እግዚእብሔር (ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ የድንጋይ ሐውልት አቆመ፤ በሐውልቱ ላይ የመጠጥ ቍርባን አፈሰሰ፤ ዘይትም አፈሰሰበት።

15. ያዕቆብም፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው።

16. ከዚያም ከቤቴል ተነሥተው ሄዱ፤ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፤ ምጡም ጠናባት።

17. ምጡ አስጨንቆአት ሳለ፣ አዋላጇ፣ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትገላገይ ነው” አለቻት።

18. እርሷ ግን ሕይወቷ ልታልፍ በማጣጣር ላይ ሳለች፣ ልጇን ቤንኦኒ አለችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው።

19. ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ በቤተልሔም ተቀበረች።

20. ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ሐውልት አቆመ፤ እስከ ዛሬም የራሔል መቃብር ምልክት ይኸው ሐውልት ነው።

21. እስራኤልም ጒዞውን በመቀጠል ከጋዴር ወንዝ ባሻገር ድንኳኑን ተከለ።

22. እስራኤልም በዚያ ምድር ሳለ፣ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋር ተኛ፤ እስራኤልም ድርጊቱን ሰማ።ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም፦

23. የልያ ልጆች፦የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል፣ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፤

24. የራሔል ልጆች፦ዮሴፍ፣ ብንያም፤

25. የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆች፦ዳን፣ ንፍታሌም፤

26. የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆች፦ጋድ፣ አሴር ናቸው።እነዚህ ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ወንዶች ልጆች ነበሩ።

27. ያዕቆብ አባቱ ወዳለበት ወደ መምሬ መጣ፤ አብርሃምና ይስሐቅ የኖሩባት፣ ቂርያት አርባቅ ወይም ኬብሮን የተባለችው ቦታ ናት።

28. ይስሐቅ መቶ ሰማንያ ዓመት ኖረ፤

ዘፍጥረት 35