ኤርምያስ 51:29-48 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. ሰው በዚያ መኖር እስከማይችል ድረስ፣የባቢሎንን ምድር ባድማ ለማድረግ፣ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ ያቀደው ስለሚጸና፣ምድር ትናወጣለች፤ በሥቃይም ትወራጫለች።

30. የባቢሎን ጦረኞች መዋጋት ትተዋል፤በምሽጎቻቸው ውስጥ ተቀምጠዋል፤ኀይላቸው ተሟጦአል፤እንደ ሴት ሆነዋል፤በማደሪያዎቿም እሳት ተለኵሶአል፤የደጇም መወርወሪያ ተሰብሮአል።

31. ከተማዪቱ ሙሉ በሙሉ መያዟን፣ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገር፣አንዱ ወሬኛ ሌላውን ወሬኛ፣አንዱ መልእክተኛ ሌላውን መልእክተኛ ወዲያው ወዲያው ይከተላል፤

32. መልካዎቿ እንደተያዙ፣የወንዝ ዳር ምሽጎቿ እንደ ተቃጠሉ፣ወታደሮቿም እንደ ተደናገጡ ሊነግሩት ይሯሯጣሉ።”

33. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የባቢሎን ሴት ልጅ በመረገጥ ላይ እንዳለ፣የእህል መውቂያ አውድማ ናት፤የመከር ወራቷም ፈጥኖ ይደርስባታል።

34. “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላን፣አድቅቆ ፈጨን፤እንደ ባዶ ማድጋ አደረገን፤እንደ ዘንዶ ዋጠን፣እንደ ጣፋጭ በልቶን ሆዱን ሞላ፤በኋላም አንቅሮ ተፋን፤

35. የጽዮን ነዋሪዎች፣ እንዲህ ይላሉ፤“በሥጋችን ላይ የተፈጸመው ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን፤”ኢየሩሳሌም እንዲህ ትላለች፤“ደማችን በባቢሎን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን።”

36. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ እሟገትልሻለሁ፣በቀልሽንም እኔ እበቀልልሻለሁ፤ባሕሯን አደርቃለሁ፣የምንጮቿንም ውሃ።

37. ባቢሎን የፍርስራሽ ክምር፣የቀበሮዎች መፈንጫ፣የድንጋጤና የመሣለቂያ ምልክት ትሆናለች፤የሚኖርባትም አይገኝም።

38. ሕዝቦቿ ሁሉ እንደ ደቦል አንበሳ ያገሣሉ፤እንደ አንበሳ ግልገልም ያጒረመርማሉ።ጒሮሮአቸው በደረቀ ጊዜድግስ አዘጋጅላቸዋለሁ፤እንዲሰክሩም አደርጋቸውና፤”

39. በሣቅ እየፈነደቁ፣ለዘላለም ላይነቁ ይተኛሉ።”ይላል እግዚአብሔር።

40. “እንደ ጠቦት፣እንደ አውራ በግና እንደ ፍየል፣ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ።

41. “ሼሻክ እንዴት ተማረከች!የምድር ሁሉ ትምክህትስ እንዴት ተያዘች!ባቢሎን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ፣ምንኛ አስደንጋጭ ሆነች።

42. ባሕር በባቢሎን ላይ ይወጣል፤ሞገዱም እየተመመ ይሸፍናታል።

43. ከተሞቿ ሰው የማይኖርባቸው፣ዝርም የማይልባቸው፣ደረቅና በረሓማ ቦታ፣ባድማ ምድርም ይሆናሉ።

44. ቤልን በባቢሎን ውስጥ እቀጣለሁ፤የዋጠውን አስተፋዋለሁ፤ሕዝቦች ከእንግዲህ ወደ እርሱ አይጐርፉም፤የባቢሎንም ቅጥር ይወድቃል።

45. “ሕዝቤ ሆይ፤ ከመካከሏ ውጡሕይወታችሁን አትርፉ!ከአስፈሪው የእግዚአብሔር ቍጣ አምልጡ።

46. ወሬ በምድሪቱ ሲሰማ፣ተስፋ አትቍረጡ፤ አትፍሩም፤ገዥ በገዥ ላይ ስለ መነሣቱ፣ዐመፅም በምድሪቱ ስለ መኖሩ፣አንድ ወሬ ዘንድሮ፣ ሌላውም ለከርሞ ይመጣል፤

47. የባቢሎንን ጣዖታት የምቀጣበት ጊዜ፣በርግጥ ይመጣልና።ምድሯ በሙሉ ትዋረዳለች፤የታረዱትም በሙሉ በውስጧ ይወድቃሉ።

48. ሰማይና ምድር በውስጣቸውም ያለው ሁሉ፣በባቢሎን ላይ እልል ይላሉ፤አጥፊዎች ከሰሜን ወጥተው፣እርሷን ይወጓታልና፤”ይላል እግዚአብሔር።

ኤርምያስ 51