ኤርምያስ 50:20-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. በእነዚያ ጊዜያት፣ በዚያ ዘመን፣”ይላል እግዚአብሔር፤“የእስራኤል በደል ይፈለጋል፤አንዳችም አይገኝም፤የይሁዳም ኀጢአት ይፈለጋል፤ከቶም የለም፤እንዲተርፉ ያደረግኋቸውን ትሩፋን እምራለሁና።

21. “የምራታይምን ምድር፣የፋቁድ ነዋሪዎችንም፣አሳዷቸው፤ ግደሏቸው፤ ፈጽማችሁም አጥፏቸው፤”ይላል እግዚአብሔር፤“ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ።

22. በምድሪቱ የጦርነት ውካታ፣የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰማ።

23. የምድር ሁሉ መዶሻ፣እንዴት ተሰበረ! እንዴትስ ደቀቀ!በሕዝቦች መካከል፣ባቢሎን እንዴት ባድማ ሆነች!

24. ባቢሎን ሆይ፤ ወጥመድ ዘርግቼልሻለሁ፤አንቺም ሳታውቂ ተይዘሻል፤ እግዚአብሔርን ተገዳድረሻልና፣ተገኘሽ፤ ተያዝሽም።

25. እግዚአብሔር የመሣሪያ ግምጃ ቤቱን ከፍቶአል፤የቍጣውን የጦር ዕቃ አውጥቶአል፤የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣በባቢሎናውያን ምድር ሥራ አለውና።

26. ከሩቅ መጥታችሁ በእርሷ ላይ ውጡ፤ጐተራዎቿን አፈራርሱ፤እንደ እህል ክምር ከምሯት፤ፈጽማችሁ አጥፏት፤ምኗም አይቅር።

27. ወይፈኖቿን ሁሉ ዕረዱ፤ወደ መታረጃም ይውረዱ!የሚቀጡበት ጊዜ፣ቀናቸው ደርሶአልና ወዮላቸው!

28. እግዚአብሔር አምላካችን የተበቀለውን፣ስለ ቤተ መቅደሱ የተበቀለውን በቀል፣ከባቢሎን የመጡ ኰብላዮችና ስደተኞች፣በጽዮን የሚናገሩትን ስሟቸው።

29. “ቀስት የሚገትሩትን፣ቀስተኞችን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩ፤አንድም ሰው እንዳያመልጥ፣ዙሪያውን ሁሉ መሽጉ፤የእስራኤልን ቅዱስ፣ እግዚአብሔርን አቃላለችና፣እንደ ሥራዋ መጠን መልሱላት፤በሌሎች ላይ እንዳደረገችውም አድርጉባት።

30. ስለዚህ ወንዶች ወጣቶቿ በየአደባባዩ ይረግፋሉ፤በዚያ ቀን ወታደሮቿ ሁሉ ይወድቃሉ፤”ይላል እግዚአብሔር፤

31. “አንተ ትዕቢተኛ፤ እነሆ፣ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤“የምትቀጣበት ጊዜ፣ቀንህ ደርሶአልና።

32. ትዕቢተኛው ይሰናከላል፤ ይወድቃልም፤የሚያነሣውም የለም፤በዙሪያው ያሉትን ሁሉ የሚበላ እሳት፣በከተሞቹ ውስጥ አስነሣለሁ።”

33. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ፣በአንድነት ተጨቍነዋል፤የማረኳቸውም ሁሉ አጥብቀው ይዘዋቸዋል፤ይለቅቋቸውም ዘንድ እንቢ ብለዋል።

34. ነገር ግን ቤዛቸው ብርቱ ነው፤ስሙም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ለምድራቸው ዕረፍትን ለመስጠት፤ተግቶ ይሟገትላቸዋል፤በባቢሎን የሚኖሩትን ግን ዕረፍት ይነሣቸዋል።

35. “ሰይፍ በባቢሎናውያን ላይ መጣ!”ይላል እግዚአብሔር፤“በባቢሎን ነዋሪዎች ላይ፤በባለ ሥልጣኖቿና በጥበበኞቿም ላይ ተመዘዘ!

ኤርምያስ 50