ኤርምያስ 49:16-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. አንተ በዐለት ንቃቃት ውስጥ የምትኖር፣የተራራውንም ከፍታ የያዝህ ሆይ፤የምትነዛው ሽብር፣የልብህም ኵራት አታሎሃል፤መኖሪያህን እንደ ንስር በከፍታ ቦታ ብትሠራም፣ከዚያ ወደ ታች እጥልሃለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

17. “ኤዶም የድንጋጤ ምልክት ትሆናለች፤ከቍስሎቿም ሁሉ የተነሣ፣በዚያ የሚያልፍ ሁሉ በመደነቅ ያላግጥባታል።”

18. በዙሪያቸው ካሉት ከተሞች ጋር፣ሰዶምና ገሞራ እንደ ተገለበጡ፣”ይላል እግዚአብሔር፤እንዲሁ ማንም በዚያ አይኖርም፤አንድም ሰው አይቀመጥባትም።

19. “አንበሳ ከዮርዳኖስ ደኖች፣ወደ ግጦሽ ሜዳ ብቅ እንደሚል፣እኔም በኤዶም ላይ ድንገት እወጣለሁ፤ ከምድሩም አባርረዋለሁ።የመረጥሁትን በእርሱ ላይ እሾማለሁ፤እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ማንስ ሊገዳደረኝ ይችላል?የትኛውስ እረኛ ሊቋቋመኝ ይችላል?

20. ስለዚህ እግዚአብሔር በኤዶም ላይ ያለውን ዕቅድ፣በቴማን በሚኖሩትም ላይ ያሰበውን አሳብ ስሙ፤ታናናሹ መንጋ ተጐትቶ ይወሰዳል፤በእነርሱም ምክንያት መሰማሪያቸውን ፈጽሞ ያጠፋል።

21. በውድቀታቸው ድምፅ ምድር ትናወጣለች፤ጩኸታቸውም እስከ ቀይ ባሕር ያስተጋባል።

22. እነሆ፤ እንደ ንስር ተወርውሮ ይወርድባታል፤ክንፎቹንም በባሶራ ላይ ይዘረጋል፤በዚያን ቀን የኤዶም ጦረኞች ልብ፣በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ልብ ይሆናል።

23. ስለ ደማስቆ፤“ክፉ ወሬ ሰምተዋልና፣ሐማትና አርፋድ ደንግጠዋል፤እንደ ተናወጠ ባሕርም ታውከዋል፤ልባቸውም ቀልጦአል።

24. ደማስቆ ተዳከመች፤ትሸሽም ዘንድ ወደ ኋላ ተመለሰች፤ብርክ ያዛት፣ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣ጭንቅና መከራ ዋጣት።

25. ደስ የምሰኝባት፣የታወቀችው ከተማ እንዴት ተተወች?

26. በርግጥ ወንዶች ወጣቶቿ በየአደባባዩ ይረግፋሉ፤በዚያ ቀን ወታደሮቿ ሁሉ ይወድቃሉ፤”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤

27. “በደማስቆ ቅጥር ላይ እሳት እለኵሳለሁ፤የወልደ አዴርንም ዐምባ ይበላል።”

28. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ ወጋቸው ስለ ቄዳርና ስለ ሐጾር መንግሥታት የተነገረ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ተነሡ፣ ቄዳርን ውጉ፤የምሥራቅንም ሕዝብ ደምስሱ።

29. ድንኳኖቻቸውና መንጎቻቸው ይወሰዳሉ፤መጠለያቸውና ግመሎቻቸው ሳይቀሩ፣ከነዕቃዎቸው ይነጠቃሉ፤ሰዎች፣ ‘ሽብር በሽብር ላይ መጥቶባቸዋል፤’እያሉ ይጮኹባቸዋል።

30. በሐጾር የምትኖሩ ሆይ፣በጥድፊያ ሽሹ በጥልቅ ጒድጓድ ተሸሸጉ፤”ይላል እግዚአብሔር፤የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በእናንተ ላይ መክሮአልና፣ወረራም ዶልቶባችኋል።

31. “ተነሡ፣ ተዘልሎ የተቀመጠውን፣በራሱ ተማምኖ የሚኖረውን ሕዝብ ውጉ፤”ይላል እግዚአብሔር፤“መዝጊያና መቀርቀሪያ በሌለው፤ለብቻው በሚኖረው ሕዝብ ላይ ዝመቱ።

ኤርምያስ 49