ኤርምያስ 14:5-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. አንዳች ሣር ባለመኖሩ፣የሜዳ አጋዘን እንኳ፣እንደ ወለደች ግልገሏን ጥላ ትሄዳለች።

6. የሜዳ አህዮች ባድማ ኰረብቶች ላይ ቆሙ፤እንደ ቀበሮም አየር ፍለጋ አለከለኩ፤ግጦሽ ባለመገኘቱ፣ዐይኖቻቸው ፈዘዙ።”

7. እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአንተ መኰብለል አብዝተናል፤በአንተም ላይ ዐምፀናል፤ኀጢአታችን ቢመሰክርብንም እንኳ፣ስለ ስምህ ብለህ አንድ ነገር አድርግልን።

8. አንተ የእስራኤል ተስፋ፤በጭንቀት ጊዜ አዳኙ፣ለምን በምድሪቱ እንደ ባዕድ፣እንደ ሌት አዳሪ መንገደኛ ትሆናለህ?

9. ግራ እንደ ተጋባ ሰው፣ለመታደግም ኀይል እንዳጣ ተዋጊ ትሆናለህ? እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በመካከላችን አለህ፤በስምህም ተጠርተናል፤እባክህ አትተወን።

10. እግዚአብሔር ስለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፤“መቅበዝበዝ እጅግ ይወዳሉ፤እግሮቻቸው አይገቱም፤ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፤አሁን በደላቸውን ያስባል፤በኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።”

11. እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ለዚህ ሕዝብ በጎነት አትጸልይ፤

12. ቢጾሙም ጩኸታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ቢያቀርቡም አልቀበላቸውም፤ ነገር ግን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር አጠፋቸዋለሁ።”

13. እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወዮ!፣ ነቢያቱ ‘ሰይፍ አታዩም፤ ራብም አያገኛችሁም፤ ነገር ግን በዚህ ስፍራ ዘለቄታ ያለው ሰላም እሰጣችኋለሁ’ ይላል ይሏቸዋል” አልሁ።

14. እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል።

15. ስለዚህ በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ ሳልልካቸው፣ ‘ሰይፍና ራብ በዚች ምድር ላይ አይመጣም’ የሚሉ እነዚህ ነቢያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤

16. ትንቢቱ የተነገረለትም ሕዝብ ከሰይፍና ከራብ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባዮች ይወድቃል፤ እነርሱንም ሆነ ሚስቶቻቸውን ወይም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቀብራቸው አይገኝም። ለበደላቸው የሚገባውንም ቅጣት በላያቸው አወርዳለሁ።

17. “ይህን ቃል እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤“ ‘ድንግሊቱ ልጄ፣ ሕዝቤ፣በታላቅ ስብራት፣በብርቱ ቍስል ተመትታለችናዐይኖቼ ቀንና ሌሊት፣ ሳያቋርጡእንባ ያፈስሳሉ

18. ወደ ገጠር ብወጣ፣በሰይፍ የተገደሉትን አያለሁ፤ወደ ከተማ ብገባ፣ በራብ የወደቁትን አያለሁነቢዩም ካህኑም፣ወደማያውቁት አገር ሸሽተዋል።’ ”

19. ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን?ነፍስህስ ጽዮንን ተጸየፈቻትን?ፈውስ እስከማይገኝልን ድረስ፣ለምን ክፉኛ መታኸን?ሰላምን ተስፋ አደረግን፤ሆኖም በጎ ነገር አላገኘንም፤የፈውስን ጊዜ ተጠባበቅን፤ነገር ግን ሽብር ብቻ ሆነ።

ኤርምያስ 14