11. “እናንተም፣ ‘እነዚህ ሰማያትንና ምድርን ያልፈጠሩ አማልክት ከምድር ላይ፣ ከሰማያትም በታች ይጠፋሉ’ ትሏቸዋላችሁ።”
12. እግዚአብሔር ግን ምድርን በኀይሉ ፈጠረ፤ዓለምን በጥበቡ መሠረተ፤ሰማያትንም በማስተዋሉ ዘረጋ።
13. ድምፁን ሲያንጐደጒድ፣ በሰማያት ያሉ ውሆች ይናወጣሉ፤ጉሙን ከምድር ዳር ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤መብረቅን ከዝናብ ጋር ይልካል፤ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።
14. እያንዳንዳቸው ጅሎችና ዕውቀት የለሾች ናቸው።ወርቅ አንጥረኛውም ሁሉ በሠራው ጣዖት ዐፍሮአል፤የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤እስትንፋስም የላቸውም።
15. እነርሱ ከንቱ የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፤ፍርድ ሲመጣባቸው ይጠፋሉ።
16. የያዕቆብ ዕድል ፈንታ የሆነው ግን እንደነዚህ አይደለም፤እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነውና፤እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው።ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
17. አንቺ የተከበብሽ፤ከያለበት ንብረትሽን ሰብስቢ፤
18. እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤“በዚህች ምድር የሚኖሩትን፣አሁን ወደ ውጪ እወነጭፋቸዋለሁ፤ጒዳቱ እንዲሰማቸው፣መከራ አመጣባቸዋለሁ፤”
19. ስለ ስብራቴ ወዮልኝ፤ቍስሌም የማይድን ነው፤ግን ለራሴ እንዲህ አልሁት፤“ይህ የኔው ሕመም ነው ልሸከመውም ይገባኛል።”