ኢያሱ 10:10-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እግዚአብሔርም የአሞራውያንን ነገሥታት በእስራኤል ፊት አሸበራቸው፤ በገባዖን እጅግ መታቸው፤ ወደ ቤትሖሮን በሚያስወጣውም መንገድ ሽቅብ ተከተላቸው፤ እስከ ዓዜቅና እስከ መቄዳም ድረስ አሳድዶ መታቸው።

11. ከቤትሖሮን ወደ ዓዜቃ ቊልቊል በሚወስደው መንገድ ላይ፣ ከእስራኤላውያን ፊት በሚሸሹበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሰማይ ትልልቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ በእስራኤላውያን ሰይፍ ካለቁት ይልቅ በወረደው የበረዶ ድንጋይ ያለቁት በልጠው ተገኙ።

12. እግዚአብሔር አሞራውያንን ለእስራኤል አሳልፎ በሰጠባት ዕለት፣ ኢያሱ እግዚአብሔርን በእስራኤል ፊት እንዲህ አለው፤“ፀሓይ ሆይ፤ በገባዖን ላይ ቁሚ፤ጨረቃም ሆይ፤ በኤሎን ሸለቆ ላይ ቀጥ በዪ፤

13. ስለዚህ ሕዝቡ ጠላቶቹን እስኪበቀልድረስ፣ ፀሓይ ባለችበት ቆመች፤ጨረቃም አልተንቀሳቀሰችም።ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል።ፀሓይ በሰማዩ መካከል ቆመች፤ ለመጥለቅም ሙሉ ቀን ፈጀባት።

14. እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ዕለት ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አልነበረም፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ተዋግቶ ነበርና።

15. ከዚያም ኢያሱ ከመላው እስራኤል ጋር ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሰ።

16. በዚህ ጊዜ አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ ዋሻ ተደብቀው ነበር።

ኢያሱ 10