1. እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ፣በቍጣው ደመና እንዴት ጋረዳት!ከሰማይ ወደ ምድር፣የእስራኤልን ክብር ወርውሮ ጣለው፤በቍጣው ቀን፣የእግሩን መቀመጫ አላስታወሰም።
2. የያዕቆብን መኖሪያ ሁሉ፣እግዚአብሔር ያለ ርኅራኄ ዋጣቸው፤የይሁዳን ሴት ልጅ ምሽጎች፣በቍጣው አፈረሳቸው፤መንግሥቷንና መሳፍንቷን፣በማዋረድ ወደ ምድር ጣላቸው።
3. በጽኑ ቍጣው፣የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ሰበረ፤ጠላት በተቃረበ ጊዜ፣ቀኝ እጁን ወደ ኋላ መለሰ፤በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳት፣በያዕቆብ ላይ የእሳት ነበልባል ነደደ።
4. እንደ ጠላት ቀስቱን ገተረ፤ቀኝ እጁ ተዘጋጅታለች፤ለዐይን ደስ የሚያሰኙትን ሁሉ፤እንደ ጠላት ዐረዳቸው፤በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን ላይ፣ቍጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ።
5. እግዚአብሔር እንደ ጠላት ሆነ፤እስራኤልንም ዋጠ፤ቤተ መንግሥቶቿን ሁሉ ዋጠ፤ምሽጎቿን አፈራረሰ፤በይሁዳ ሴት ልጅ፣ለቅሶንና ሰቈቃን አበዛ።
6. ማደሪያውን እንደ አትክልት ስፍራ ባዶ አደረገ፤መሰብሰቢያ ስፍራውን አፈረሰ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን፣ዓመት በዓላቶቿንና ሰንበታቷን እንድትረሳ አደረጋት፤በጽኑ ቍጣው፣ንጉሡንና ካህኑን እጅግ ናቀ።
7. እግዚአብሔር መሠዊያውን ናቀ፤መቅደሱንም ተወ፤የቤተ መንግሥቶቿን ቅጥሮች፣ለጠላት አሳልፎ ሰጠ፤በዓመት በዓል ቀን እንደሚደረገው በእግዚአብሔር ቤት በኀይል ጮኹ።