ማርቆስ 12:35-44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ?

36. ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ጌታ ጌታዬን፣ ‘ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው።” ይላል፤

37. ታዲያ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ካለው፣ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር።

38. በሚያስተምርበትም ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ የተንዘረፈፈ ቀሚስ ለብሰው መዞርን ይወዳሉ፤ በየአደባባዩም የአክብሮት ሰላምታ ይሻሉ፤

39. በምኵራብ ከፍተኛውን ወንበር፣ በግብዣም ቦታ የከበሬታን ስፍራ ይፈልጋሉ፤

40. በረጅም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቍታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።”

41. ኢየሱስ በገንዘብ ማስቀመጫው አንጻር ተቀምጦ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ገንዘብ ማስቀመጫ ሣጥን ሲያስ ገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤

42. አንዲት ምስኪን መበለት ግን ከአንድ ሳንቲም የማይበልጡ ሁለት የናስ ቤሳዎች አስገባች።

43. ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህቺ ድኻ መበለት ሣጥኑ ውስጥ ከጣሉት ከሌሎቹ የበለጠ አስገባች።

44. እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን በድኽነት ዐቅሟ ያላትን ሁሉ አውጥታ ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ ሰጠች።”

ማርቆስ 12