መዝሙር 57:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ማረኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ማረኝ፤ነፍሴ አንተን መጠጊያ አድርጋለችና፤በክንፎችህ ሥር እጠለላለሁ።

2. ለእኔ ያሰበውን ወደሚፈጽምልኝ አምላክ፣ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ።

3. ከሰማይ ልኮ ያድነኛል፤የረገጡኝን ያዋርዳቸዋል፤ ሴላእግዚአብሔር ምሕረቱንና ታማኝነቱን ይልካል።

4. ነፍሴ በአንበሶች ተከብባለች፤በሚዘነጣጥሉ አራዊት መካከል ወድቄአለሁ፤እነዚህም፣ ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፣ምላሳቸውም የተሳለ ሰይፍ የሆኑ ሰዎች ናቸው።

5. እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትስፈን።

6. ለእግሬ ወጥመድን ዘረጉ፤ነፍሴንም አጐበጧት፤በመተላለፊያዬ ላይ ጒድጓድ ቈፈሩ፤ነገር ግን ራሳቸው ገቡበት። ሴላ

7. እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤ልቤ ጽኑ ነው፤እቀኛለሁ፤ አዜማለሁ።

8. ነፍሴ ሆይ፤ ንቂ!በገናና መሰንቆም ተነሡእኔም በማለዳ እነሣለሁ።

9. ጌታ ሆይ፤ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤በሰዎችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤

10. ምሕረትህ እስከ ሰማያት ከፍ ብላለችና፤ታማኝነትህም እስከ ደመናት ትደርሳለች።

11. እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትስፈን።

መዝሙር 57