መዝሙር 40:4-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እግዚአብሔርን መታመኛው ያደረገ፣ወደ ትዕቢተኞች የማይመለከት፣የሐሰት አማልክትን ወደሚከተሉት የማያይ፣ሰው ብፁዕ ነው።

5. እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ለእኛ ያቀድኸውን፣ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤ላውራው ልናገረው ብል፣ስፍር ቍጥር አይኖረውም።

6. መሥዋዕትንና ቊርባንን አልፈለግህም፤ጆሮቼን ግን ከፈትህ፤የሚቃጠል መሥዋዕትን፣የኀጢአትንም መሥዋዕት አልሻህም።

7. እኔም እንዲህ አልሁ፤ “እነሆ፤ መጥቻለሁ፤ስለ እኔ በመጽሐፍ ተጽፎአል፤

8. አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ።”

9. በታላቅ ጉባኤ ውስጥ ጽድቅን አበሠርሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ እንደምታውቀው፣ከንፈሮቼን አልገጠምሁም።

10. ጽድቅህን በልቤ አልሸሸግሁም፤ታማኝነትህንና ማዳንህን እናገራለሁ፤ምሕረትህንና እውነትህን፣ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም።

11. እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህን አትንፈገኝ፤ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ፤

12. ስፍር ቍጥር የሌለው ክፋት ከቦኛልና፤የኀጢአቴ ብዛት ስለ ያዘኝ ማየት ተስኖኛል፤ከራሴ ጠጒር ይልቅ በዝቶአል፤ልቤም ከድቶኛል።

13. እግዚአብሔር ሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

14. ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ፣ይፈሩ፤ ይዋረዱም፤ጒዳቴንም የሚሹ፣ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ።

15. በእኔ ላይ፣ “እሰይ! እሰይ!” የሚሉ፣በራሳቸው እፍረት ይደንግጡ።

16. አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስ ይበላቸው፤ዘወትር የአንተን ማዳን የሚወዱ፣ “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል” ይበሉ።

17. እኔ ድኻና ችግረኛ ነኝ፤ጌታ ግን ያስብልኛል።አንተ ረዳቴና አዳኜ ነህ፤አምላኬ ሆይ፤ አትዘግይ።

መዝሙር 40