መዝሙር 38:7-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ወገቤ እንደ እሳት ነዶአል፤ሰውነቴም ጤና የለውም።

8. እጅግ ዝያለሁ፤ ፈጽሞም ደቅቄአለሁ፤ከልቤም መታወክ የተነሣ እጮኻለሁ።

9. ጌታ ሆይ፤ ምኞቴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነው፤ጭንቀቴም ከአንተ የተሰወረ አይደለም።

10. ልቤ በኀይል ይመታል፤ ጒልበት ከድቶኛል፤የዐይኔም ብርሃን ጠፍቶአል።

11. ከቊስሌ የተነሣ ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ሸሹኝ፤ጎረቤቶቼም ርቀው ቆሙ።

12. ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ሊያጠፉኝ ዛቱ፤ቀኑንም ሙሉ ተንኰል ይሸርባሉ።

13. እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቈሮ፣አፉንም መክፈት እንደማይችል ዲዳ ሆንሁ።

14. በእርግጥም ጆሮው እንደማይሰማ፣አንደበቱም መልስ መስጠት እንደማይችል ሰው ሆንሁ።

15. እግዚአብሔር ሆይ፤ በተስፋ እጠብቅሃለሁ፤ጌታ አምላኬ ሆይ፤ አንተ መልስ ትሰጠኛለህ።

16. እኔ፣ “ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ አይበላቸው፤እግሬም ሲንሸራተት፣ በላዬ አይኵራሩብኝ” ብያለሁና።

17. ልወድቅ ተቃርቤአለሁ፤ከሥቃዬም ከቶ አልተላቀቅሁም።

18. በደሌን እናዘዛለሁ፤ኀጢአቴም አውካኛለች።

19. ብርቱዎች ጠላቶቼ ብዙ ናቸው፤ያለ ምክንያት የሚጠሉኝም ስፍር ቊጥር የላቸውም።

መዝሙር 38