1. በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖንና ስፍር ቍጥር ለሌለው ሕዝቡ እንዲህ በል፤“ ‘በክብር ከአንተ ጋር ማን ሊወዳደር ይችላል፤
3. ለጫካው ጥላ የሆኑ የሚያማምሩ ቅርንጫፎች የነበሩትን፣እጅግ መለሎ ሆኖ፣ጫፉ ሰማይ የደረሰውን፣የሊባኖስን ዝግባ አሦርን ተመልከት።
4. ውሆች አበቀሉት፤ጥልቅ ምንጮች አሳደጉት፤ጅረቶቻቸው ፈሰሱ፤የሥሮቹንም ዙሪያ ሁሉ አረሰረሱ፤በመስኩ ላይ ወዳሉት ዛፎች ሁሉ፣መስኖዎቻቸውን ለቀቁት።
5. ስለዚህ በደን ካሉት ዛፎች ሁሉ፣እጅግ ከፍ አለ፤ቅርንጫፎቹ በዙ፤ቀንበጦቹ ረዘሙ፤ከውሃውም ብዛት የተነሣ ተስፋፉ።
6. የሰማይ ወፎች ሁሉ፣በቅርንጫፎቹ ላይ ጐጆአቸውን ሠሩ፤የምድር አራዊት ሁሉ፣ከቅርንጫፎቹ ሥር ግልገሎቻቸውን ወለዱ።ታላላቅ መንግሥታትም ሁሉ፣ከጥላው ሥር ኖሩ።
7. ከተንሰራፉት ቅርንጫፎቹ ጋር፣ውበቱ ግሩም ነበር፤ብዙ ውሃ ወዳለበት፣ሥሮቹ ጠልቀው ነበርና።
8. በእግዚአብሔር ገነት ያሉ ዝግባዎች፣ሊወዳደሩት አልቻሉም፤የጥድ ዛፎች፣የእርሱን ቅርንጫፎች አይተካከሉትም፤የአስታ ዛፎችም፣ከእርሱ ቅርንጫፎች ጋር አይወዳደሩም፤በእግዚአብሔር ገነት ያለ ማናቸውም ዛፍ፣በውበት አይደርስበትም።
9. በብዙ ቅርንጫፎች፣ውብ አድርጌ ሠራሁት፤በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ፣በገነት ያሉትን ዛፎች የሚያስቀና አደረግሁት።
10. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጥቅጥቅ ባለው ቅጠል ላይ ጫፉን ከፍ በማድረግ ራሱን በማንጠራራቱ፣ በርዝማኔውም በመኵራራቱ፣