1. በሰባተኛው ዓመት ዮዳሄ በረታ፤ የመቶ አለቆች ከሆኑት ከይሮሐም ልጅ ከዓዛርያስ፣ ከይሆሐናን ልጅ ከይስማኤል፣ ከዖቤድ ልጅ ከዓዛርያስ፣ ከዓዳያ ልጅ ከማዕሤያ፣ ከዝክሪ ልጅ ከኤሊሳፋጥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
2. እነርሱም ወደ መላው ይሁዳ ሄደው፣ ሌዋውያንንና የእስራኤል ቤት አለቆችን ከየከተማው ሁሉ ሰበሰቡ። ወደ ኢየሩሳሌም በመጡ ጊዜም፣
3. ጉባኤው ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ከንጉሡ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ።ዮዳሄም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ለዳዊት ዘር በሰጠው ተስፋ መሠረት እነሆ፣ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል።
4. እንግዲህ እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ዕለት ተረኛ ከሆናችሁት ከእናንተ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ አንድ ሦስተኛው በሮቹን ጠብቁ፤
5. አንድ ሦስተኛው ቤተ መንግሥቱን፣ አንድ ሦስተኛው “የመሠረት ቅጽር በር” የተባለውን ጠብቁ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ይሁኑ።
6. ተረኛ ከሆኑት ካህናትና ሌዋውያን በቀር ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይግባ፤ እነርሱ የተቀደሱ ስለሆኑ ይግቡ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ ግን፣ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዳይገቡ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይጠብቁ።
7. ሌዋውያኑም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ይቁሙ፤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገባ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ንጉሡ በሚሄድበትም ቦታ ሁሉ አብረውት ይሁኑ።”
8. ሌዋውያኑና ይሁዳ ሁሉ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዘው አደረጉ፤ ካህኑ ዮዳሄ ከጥበቃ ክፍሎች የትኛውንም አላሰናበተም ነበርና፣ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሥራ ላይ የሚሰማሩትንና ከሥራ የሚወጡትን የራሱን ሰዎች ወሰደ፤