8. ኢዮአካዝ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
9. ኢዮአካዝ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ። ልጁ ዮአስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
10. በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ዘመን፣ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ስድስት ዓመትም ገዛ።
11. እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት ሁሉ አልራቀም፤ በዚያው ገፋበት።
12. ዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላ ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያካሄደው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?።
13. ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓም በእግሩ ተተክቶ በዙፋኑ ተቀመጠ። ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ።
14. በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ ለሞት ባደረሰው ሕመም ታሞ ያጣጥር ነበር። የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ወርዶ አለቀሰለት፤ “ወየው አባቴን! ወየው አባቴን! ወየው የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” እያለም ጮኸ።
15. ኤልሳዕም፣ “አንድ ቀስትና ፍላጾች አምጣ” አለው፤ እርሱም አመጣ፤
16. የእስራኤልንም ንጉሥ፣ “ቀስቱን በእጅህ ያዘው” አለው፤ ቀስቱን በያዘውም ጊዜ ኤልሳዕ እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ።
17. ቀጥሎም፣ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለው፤ ከፈተውም፤ ኤልሳዕም፣ “በል አስፈንጥረው” አለው፤ አስፈነጠረውም፤ ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር የድል ቀስት!” ሶርያ ድል የምትሆንበት ቀስት!” አለ። ኤልሳዕም እንደ ገና “ሶርያውያንንም አፌቅ ላይ ፈጽመህ ድል ታደርጋቸዋለህ” አለው።
18. ቀጥሎም፣ “በል ቀስቶቹን ውሰድ” አለው፤ ንጉሡም ወሰደ። ኤልሳዕም፣ “መሬቱን ውጋ” አለው። እርሱም ሦስት ጊዜ ወግቶ አቆመ።
19. የእግዚአብሔርም ሰው ተቈጣውና፣ “መሬቱን አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መውጋት ነበረብህ፤ እንዲህ ብታደርግ ኖሮ ሶርያን ታሸንፍና ፈጽመህ ትደመስሳት ነበር፤ አሁን ግን የምታሸንፈው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው” አለው።
20. ኤልሳዕ ሞተ፤ ቀበሩትም። በዚህም ጊዜ ሞዓባውያን አደጋ ጣዮች በየዓመቱ በጸደይ ወራት ወደ እስራኤል ምድር እየሰረጉ ይገቡ ነበር።
21. አንድ ጊዜ እስራኤላውያን ሰው ሞቶ ሲቀብሩ፣ አንድ የአደጋ ጣይ ቡድን በድንገት አዩ፤ ስለዚህ የሞተውን ሰው ሬሳ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ጣሉት፤ ሬሳው የኤልሳዕን ዐፅም እንደ ነካም ወዲያውኑ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ።
22. በኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ሁሉ፣ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል፣ እስራኤልን ያስጨንቃቸው ነበር።
23. እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፤ አዘነላቸው፤ ፊቱን መለሰላቸው፤ ይህም ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ስለ ገባው ኪዳን ሲል ነው፤ እስከ ዛሬ ድረስ ሊያጠፋቸው አልፈለገም፤ ከፊቱም አላስወገዳቸውም።
24. የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁ ቤንሃዳድም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
25. ከዚያም የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ፣ አዛሄል ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በጦርነት የወሰዳቸውን ከተሞች ከአዛሄል ልጅ ከቤን ሃዳድ አስመልሶ ያዘ። ዮአስ ሦስት ጊዜ ድል አደረገው፤ የእስራኤልንም ከተሞች በዚህ ሁኔታ መልሶ ያዘ።