44. እርሱም፣ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፣ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው።
45. ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት አምላክ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።
46. እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቈር ጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፣ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ መኖሩን ያውቃል።
47. እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ሰልፉ የእግዚአሔር ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።”
48. ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፣ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ።
49. እጁንም ወደ ኮሮጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ ፍልስጥኤማዊውም በግምባሩ ተደፋ።
50. በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም።
51. ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቈረጠው።ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ።
52. ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እየፎከሩ ፍልስጥኤማውያንን እስከ ጌት መግቢያና እስከ ዔቅሮን በሮች ድረስ አሳደዷቸው። የፍልስጥኤማውያንም ሬሳ ከሸዓይራይም አንሥቶ እስከ ጌት ከዚያም እስከ ዔቅሮን በሮች ባለው መንገድ ላይ ወድቆ ነበር።
53. እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሱ፤ ሰፈራቸውንም በዘበዙ።
54. ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማዊውን የጦር መሣሪያዎች በራሱ ድንኳን ውስጥ አስቀመጠ።
55. ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ለመግጠም በሚሄድበት ጊዜ ሳኦል ተመልክቶ የሰራዊቱን አዛዥ አበኔርን፣ “አበኔር ሆይ፤ ይህ ልጅ የማን ነው?” ሲል ጠየቀው።አበኔርም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አላውቅም” ብሎ መለሰለት።
56. ንጉሡም፣ “እንግዲህ ወጣቱ የማን ልጅ እንደሆነ ተከታትለህ ድረስበት” አለው።