1 ሳሙኤል 15:14-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ሳሙኤል ግን፣ “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።

15. ሳኦልም፣ “ሰራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው፤ የቀሩትን ግን በሙሉ አጥፍተናል” ብሎ መለሰ።

16. ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “ስማ! ትናንት ማታ እግዚአብሔር የነገረኝን ልንገርህ?” አለው።ሳኦልም፣ “ንገረኝ” ሲል መለሰለት።

17. ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “በዐይንህ ፊት ታናሽ የነበርህ ብትሆንም፣ የእስራኤል ነገዶች መሪ ሆነህ የለምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል።

18. እግዚአብሔርም፣ ‘ሄደህ እነዚያን ኀጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ጨርሰህ እስክታጠፋቸውም ድረስ ውጋቸው’ ብሎ ልኮህ ነበር።

19. ታዲያ እግዚአብሔርን ለምን አልታዘዝህም? ለምርኮውስ ተስገብግበህ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ለምን አደረግህ?”

20. ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ታዝዣለሁ፤ እግዚአብሔር በላከኝ መሠረት ሄጃለሁ፤ አማሌቃውያንን በሙሉ አጥፍቼ ንጉሣቸውን አጋግን አምጥቻለሁ።

21. ሰራዊቱ ግን ከምርኮው ለእግዚአብሔር ከተለዩት መካከል፣ ምርጥ ምርጡን በግና በሬ፣ በጌልገላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ወስደዋል።”

22. ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤“ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን?እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል።

23. ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።”

24. ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን መመሪያ ጥሻለሁ፤ ሕዝቡን ፈርቼ ስለ ነበር፣ የጠየቁኝን ታዝዣለሁ።

25. አሁንም፣ ኀጢአቴን ይቅር እንድትለኝ፣ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ አብረኸኝ እንድትመለስ እለምንሃለሁ።”

26. ሳሙኤል ግን፣ “ከአንተ ጋር አልመለስም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃል፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል” አለው።

27. ሳሙኤል ለመሄድ ዘወር ባለ ጊዜ፣ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፤ ተቀደደም።

28. ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀዶታል፤ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጥቶታል።

29. የእስራኤል ክብር የሆነው እግዚአብሔር አይዋሽም፤ አይጸጸትምም፤ እርሱ ይጸጸት ዘንድ ሰው አይደለምና።”

1 ሳሙኤል 15