ዘፍጥረት 40:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እነርሱም “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጒምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት።ዮሴፍም፣ “ሁልጊዜስ ቢሆን የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሚገኝ አይደለምን? እስቲ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው።

9. ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል አየሁ፤

10. ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው አቈቊጣ አበበች፤ ዘለላዎቿም ተንዠርግገው በሰሉ።

11. የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።”

12. ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤

13. በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፣ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደነረው ሁሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጠለህ።

14. እንግዲህ፣ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፣ እኔን አስበህ ቸርነት አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤

15. ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በአፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።”

16. የእንጀራ ቤት አዛዡም፣ ለመጠጥ አላፊዎቹ አለቃ ሕልም፣ የተሰጠው ፍቺ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፣ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፤ ሦስት መሶቦች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤

17. በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፤ ወፎችም ራሴ ላይ ካለው መሶብ ይበሉ ነበር።”

18. ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤

19. በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።”

20. በሦስተኛውም ቀን የፈርዖን የልደት በዓል ነበረ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብር አበላ። በዚያኑ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎችን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምቱ ካሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው።

ዘፍጥረት 40